የሻምበል ለገሰ አስፋው የቀብር ስነ ስርዓት ተፈጸመ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 20/2011)የቀድሞ የደርግ መንግስት የኢሰፓ ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩት የሻምበል ለገሰ አስፋው የቀብር ስነ ስርዓት ተፈጸመ።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የቀድሞው አፈጉባኤ ዳዊት ዩሐንስ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ተሰምቷል።

የአፄ ሃይለስሴን መንግስት ከስልጣን ለማውረድ ከተንቀሳቀሱት የደርግ አባላት አንዱ የነበሩትና በኋላም በኢሰፓ ውስጥ ከ7ቱ ቁልፍ ባለስልጣናት አንዱ የነበሩት ሻምበል ለገሰ አስፋው በህክምና ሲረዱ ቆይተው ህይወታቸው ያለፈው በሳምንቱ መጨረሻ መሆኑ ታውቋል።

የደርግ መንግስት ከስልጣን ከተወገደ በኋላ ወደ እስር ቤት ከተጋዙት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት አንዱ የነበሩት ሻምበል ለገሰ አስፋው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ሞት ከተፈረደባቸው ባለስልጣናትም አንዱ ነበሩ።

በሃይማኖት አባቶችና በሃገር ሽማግሌዎች ተማፅኖ መንግስት የሞት ፍርዱ ወደ ዕድሜ ልክ እንዲቀየር በመወሰኑ በህግ መሰረት የእስራት ጊዜያቸውን በአመክሮ ጨርሰው ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር ተፈተዋል።

በቀድሞ ሸዋ ክፍለ ሃገር በመናገሻ አውራጃ መስከረም 21 ቀን 1935 የተወለዱት ሻምበል ለገሰ አስፋው በ76 ዓመታቸው ባለፈው አርብ ህይወታቸው አልፏል።

ትናንት ዕሁድ በቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስና ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሻለቃ ፍሰሃ ደስታ በተገኙበት የቀብር ስነ-ስርዓታቸው ተፈፅሟል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ የነበሩት አቶ ዳዊት ዩሐንስ በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ ሕይወታቸው ማለፉ ተሰምቷል።

ከ1987 እስከ 1989 ለ12 ዓመታት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ የነበሩት አቶ ዳዊት ዩሐንስ በህክምና ሲረዱ ቆይተው ህይወታቸው ማለፉን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልጿል።

የምክር ቤቱ አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎም የሃዘን መግለጫ አስተላልፈዋል።

የአቶ ዳዊት ዩሐንስ የቀብር ስነ-ስርዓት መቼና የት እንደሚፈጸም የተገለጸ ነገር ግን የለም።