የሶማሌ ክልል የፍትህ ጥምረት የፖለቲካ ንቅናቄ ተመሰረተ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 22/2010)የሶማሌ ክልል የፍትህ ጥምረት የተሰኘ የፖለቲካ ንቅናቄ በይፋ ተመሰረተ።

ጥምረቱ በአሜሪካ ሚኒሶታ ግዛት የምስረታ ጉባዔውን አካሂዷል።

በሶማሌ ክልል እየተፈጸመ ያለውን መጠነ ሰፊ ጭቆና ከሌሎች የኢትዮጵያ ሃይሎች ጋር በመሆን ይታገላል ይላል በይፋ የወጣው የጥምረቱ ጋዜጣዊ መግለጫ።

ፋይል

የተበታተነውን የሶማሌ ክልል ተወላጆች ትግል ወደአንድ የተጠናከረ ሃይል በማምጣት ለፍትህና ነጻነት መስፈን ከምንጊዜውም በላይ በአንድነት ለመታገል መዘጋጀቱንም ጥምረቱ አስታውቋል።

በሚኒሶታ ሚኒያፖሊስ የሶማሌ ክልል የፍትህ ጥምረት ምስረታ የሁለት ዓመት ቅድመ ዝግጅት ካደረገ በኋላ እውን የሆነ ነው።

ባለፈው ዓመት ጥምረቱ የተቋቋመ ቢሆንም በይፋ ምስረታ በዓሉን በማካሄድ ወደ ስራ የገባው ባለፈው ቅዳሜ በሚኒሶታ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ነው።

በታህሳስ ወር በኬኒያ ናይሮቢ የጥምረቱ መስራች ጉባዔ ስብሰባ የተካሄደ ሲሆን የተበታተነውን የሶማሌ ክልል ተወላጆችን ትግል በአንድነት ለማስተባበር የጥምረቱን መመስረት አስፈላጊነት ታምኖበት መመስረቱ ተገልጿል።

በተለይም በክልሉ በአሁኑ ጊዜ እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ ንቅናቄ ምስረታው የተለየ ገጽታ እንዲኖረው አድርጎታል።

የሶማሌ ክልል የፍትህ ጥምረት የሶማሌ ክልል ተወላጆችን በማስተባበር እውነተኛ አስተዳደርና የፍትህ መረጋጋጥ ሰፍኖ ማየት እንደሆነ በምስረታ በዓሉ ላይ ተገልጿል።

የሶማሌ ክልል የፍትህ ጥምረት እንዳለው የሶማሌ ክልል ተወላጆች ስቃይና መከራ እየተባባሰ መጥቷል።

ምንም እንኳን ባለፉት ስርዓተ መንግስታት ጭቆናው የነበረ ቢሆንም አሁን በስልጣን ላይ ባለው አገዛዝ የሶማሌ ክልል ህዝብ የከፋ ዘመን ላይ ይገኛል ይላል የጥምረቱ መግለጫ።

በተለይም የኢህአዴግ አገዛዝ ቀኝ እጅ በሆነው የአብዲ ኢሌ አስተዳደር የክልሉ ተወላጆች ከፍተኛ ስቃይ እየደረሰባቸው እንደሆነ የሚገልጸው ጥምረቱ ይህን ስቃይና መከራ እጅን አጣጥፎ በዝምታ በመመልከት የሚቆም አይደለም ሲል ገልጿል።

ለችግሩ መባባስ ከጨቆኙ አገዛዝ ሌላ እኛም ተጠያቂ መሆናችን አይቀርምም ብሏል።

ይህ ስቃይ እንዲቆም ያደርግነው ጥረት የለም ወይም ውጤታማ አይደለም በማለት ራሱን ከጠያቂነት ነጻ እንደማያደርግ ጥምረቱ አስታውቋል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የሶማሌ ክልል ህዝብ እያደረገ ያለውን ትግል እንደምቹ አጋጣሚ በመውሰድ ውጤታማ የሆነ የተቀናጀ የትግል ስትራቴጂ መዘርጋት አለበት ሲልም ጥሪ አድርጓል።

በምስረታ በዓሉ ላይ የትግሉ አጋር የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ድርጅቶች በእንግድነት የተገኙ ሲሆን ለጥምረቱ ድጋፋቸውን ማሳየታቸው ተገልጿል።

የሶማሌ ክልል የፍትህ ጥምረት ከሌሎች በሶማሌ ህዝብ ስም ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች በተለየ ሁኔታ ከኢትዮጵያውያን ጋር በአንድነት ለመስራት የተዘጋጀ እንደሆነ ይነገራል።

በምስረታው ላይ እንደተገለጸው ኢሳትን ጨምሮ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ጋር በቅርበት በመስራት በክልሉ ያለውን የህዝብ ትግል መረጃዎችን በማስተላለፍ ትግሉ ለማጠናከር ዓላማ አድርጎ መነሳቱን አስታውቋል።

በኢትዮጵያ ፍትህና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን በማድረግ የሶማሌ ክልል ህዝብ በእኩልነት የሚኖርበት ሀገር እንዲሆን የሚችለውን እንደሚያደርግም ከምስረታው መግለጫ መረዳት ተችሏል።