የሶማሌ ክልል በጀት በከፍተኛ መጠን ሲዘረፍ ነበር ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 17/2011) የሶማሌ ክልል በጀት በህወሃት ባለስልጣናትና ባለሃብቶች በከፍተኛ መጠን ሲዘረፍ ነበር ተባለ።

በኮንትራት ተቋራጭነት ስም የህወሃት ባለስልጣናት በቢሊየን የሚቆጠር የክልሉን በጀት ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች መውሰዳቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ሰሞኑን በተለያዩ ዞኖች ባደረጉት የስራ ጉብኝት ወቅት ክልሉ ከፍተኛ የበጀትና የመሬት ዘረፋ እንደተፈጸመበት ማረጋገጣቸውን ነው የፕሬዝዳንቱ የህግ አማካሪ ለኢሳት የገለጹት።

ሜቴክ የ1ቢሊየን ብር ፕሮጀክት ተዋውሎ ገንዘቡን በሙሉ መውሰዱንና ስራውን ግን አለማስረከቡ ተረጋግጧል።

በአንድ ዞን ብቻ ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በህወሃት የጦር ሹማምንት ተይዞ ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር እንደተወሰደበትም የፕሬዝዳንቱ የህግ አማካሪ ገልጸዋል።

ሰሞኑን የሶማሌ ክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፋ ዑመር ወደ ምስራቁ ጠረፍ ወደ ሚገኙ የክልሉ ዞኖች የስራ ጉብኝት አድርገው ነበር።

የኢሳት የመረጃ ምንጮች እንደገለጹት የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት የህወሃት አገዛዝ ባለስልጣናት በክልሉ መጠነ ሰፊ የበጀትና የመሬት ዘረፋ መፈጸማቸውን ያረጋገጠ ሆኗል።

ባለፉት 10 ዓመታት ለክልሉ የሚሰጠው ዓመታዊ በጀት በፕሮጀክት ስም የህወሀት ባለስልጣናት ኪስ እንደሚገባ ነው በየዞኖቹ በተካሄደው ጉብኝት ወቅት ለማረጋገጥ የተቻለው።

አቶ ጀማል ዲሪዬ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የህግ አማካሪ ለኢሳት እንደገለጹት የበጀት ዘረፋው በምርመራ ላይ ቢሆንም ፍንጮች የሚያመላክቱት የህወሀት ባልስልጣናት በርካታ ቢሊዮን የሚገመት ገንዘብ በተቋራጭ ስም ዘርፋዋል።

የሶማሌ ክልል በጀትን በመቀራመት ከፍተኛ ዘረፋ ከፈጸሙ ተቋማት ደግሞ በህወሀት ጄነራሎች ይመራ የነበረው ሜቴክ ዋናው እንደነበር ነው አቶ ጀማል ዲሪዬ የሚገልጹት። ሜቴክ ለህዝብ ጥቅም ላልዋለ ፕሮጀክት 1ቢሊየን ብር ወስዷል።

በሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የሰሞኑ ጉብኝት ከህዝቡ የተሰማው ሌላው መጠነ ሰፊ ዘረፋ በመሬት ላይ የተፈጸመ ነው ተብሏል።

የፕሬዝዳንቱ የህግ አማካሪ አቶ ጀማል ዲሪዬ እንደሚሉት በሸበሌ ዞን ብቻ ከ100ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመከላከያ የጦር ሹማምንት ተይዞ ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር ሲወሰድበት ቆይቷል።

አቶ ጀማል ያገኘነው መረጃ የአንድ ዞን ነው በሌሎቹ የተፈጸመውን ዘረፋ ከተመለከትን አስደንጋጭ ሊሆን ይችላል ባይ ናቸው። ምርመራው ሲጠናቀቅ ሙሉ መረጃው እንደሚታወቅም ገልጸዋል።

በሶማሌ ክልል በተፈጸመው የመሬት ዘረፋ ላይ ህብረተሰቡ መረጃ በመስጠት ትብብር እያደረገ ነው።

በዘረፋው ላይ የተሰማሩትን በተመለከተም ከህብረተሰቡ የተደበቀ ባይኖርም በምርመራ እስኪረጋገጥ ድረስ ይፋዊ የሆነ መረጃ መስጠት እንደማይቻል ነው የፕሬዝዳንቱ የህግ አማካሪ የሚገልጹት።

በህብረተሰቡ ከሚጠቀሱና በመሬት ዘረፋው ላይ ከተሰማሩ የህወሀት ባለስልጣናት መሀል የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የአቶ መለስ ዜናዊ ቤተሰብ እንደሚገኝበት ተጠቅሷል።

አቶ ጀማል ዲሪዬ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የህግ አማካሪ ለኢሳት እንደገለጹት የተዘረፉ መሬቶችን በማስመለስ ለህዝቡ መልሶ የመስጠት ስራ በቅርቡ ይጀመራል።

ከፍተኛ መጠን ያለው የበጀትና የመሬት ዘረፋ በሚከናወንበት ሶማሌ ክልል ወ 500ሺህ የሚጠጋ ህዝብ በረሃብና ድርቅ የተነሳ ተፈናቅሎ በካምፕ ተጠልሎ እንደሚገኝ በቅርቡ መገልጹ የሚታወስ ነው።