የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አባል ታሰሩ

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 5/2010) የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አባል በአብዲ ዒሌ ታጣቂዎች መታሰራቸው ተገለጸ።

የምክር ቤት አባሉ አቶ አብዲ አብዱላሂ ሁሴን የታሰሩት የክልሉ ምክር ቤት እየሄደበት ያለው አካሄድን በተመለከተ ማብራሪያ የሚጠይቅ ደብዳቤ ከጻፉ በኋላ መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ይቅር እንባባል የሚል መግለጫ ትላንት የሰጡት የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ ዛሬ የምክር ቤት አባሉን ማሰራቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

አቶ አብዲ ዒሌ የቀድሞውን ደህንነት ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋን በሶማሌ ክልል ለተፈጸሙ ግድያዎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂ በማድረግም መግለጫ ሰጥተዋል።

አቶ አብዲ አብዱላሂ ሁሴን ከክልሉ ምክር ቤት ቅጥር ግቢ በታጣቂዎች የተወሰዱት ዛሬ ጠዋት ነው።

ለኢሳት በደረሰው መረጃ ላይ እንደተመለከተው በሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ ዑመር ዒሌ ጠያቂነት በምክር ቤቱ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ የተደረጉት አቶ አብዲ አብዱላሂ ሁሴን በቁጥጥር ስር ውለው ወደ እስር ቤት ተወስደዋል።

በሶማሌ ክልል ምክር ቤት ውስጥ ከሚገኙ አባላት በትምህርት ደረጃና በልምድ የተሻለ ቦታ የደረሱ ናቸው የሚባልላቸው አቶ አብዲ አብዱላሂ በክልሉ የሚፈጸሙትን ግድያዎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በተመለከተ በየጊዜው ቅሬታቸውን የሚያሰሙ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።

በክልሉ ለውጥ እንደሚያስፈልግ፣ በመላ ሀገሪቱ ከሚታየው ጅምር የለውጥ ሂደት ጋር አብሮ መራመድ ያስፈልጋል በማለት የሚሰጡት አስተያየት በአብዲ ዒሌ በኩል እንደስጋት መታየቱን ነው የኢሳት ምንጮ የሚገልጹት።

ትላንት በነበረው የምክር ቤቱ ስብሰባ አካሄዱንና አጀንዳውን በተመለከተ ማብራሪያ የሚጠይቅ ደብዳቤ ማቅረባቸውን የጠቀሱት የኢሳት ምንጮች ዛሬ ሁለተኛውን ቀን ስብሰባ ለመካፈል ወደ ምክር ቤቱ ሲያመሩ በታጣቂዎች ተይዘው መታሰራቸው ተገልጿል።

አቶ አብዲ አብዱላሂ ከተያዙ በኋላ ወደየት እንደተወሰዱ አለመታወቁንና አሁን ያሉበት ሁኔታ ግልጽ እንዳልሆነ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በተያያዘ ዜና በቅርቡ በሂውማን ራይትስ ዎች የወጣውን ሪፖርት እንዲያስተባብሉ በአብዲ ዒሌ ማስፈራሪያ የተሰጣቸውና በጄል ኦጋዴን እስር ቤት ከፍተኛ ማሰቃየት የደረሰባቸው አቶ ሙሀመድ አኑ የተባሉ የሶማሌ ክልል ተወላጅ ህይወታቸው አደጋ ላይ መውደቁን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

አቶ መሀሙድ በጄል ኦጋዴን በነበረው የእስር ቆይታቸው ምንም ዓይነት ድብደባ እንዳልተፈጸመባቸውና የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ሀሰት ነው በማለት በቢቢሲ ሶማልኛ ፕሮግራም ላይ ቀርበው እንዲናገሩና ያን ካላደረጉ ወደ እስር ቤት ተመልሰው እንደሚገቡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ተብሏል።

እሳቸው ግን በተጠቀሰው ሚዲያ ቀርበው ውሸት አልናገርም በማለት አብዲ ዒሌን ማጋለጣቸውን ነው ያገኘነው መረጃ የሚያመለክተው።

በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ ተደብቀው የሚገኙት አቶ መሃሙድ ለህይወታቸው እንደሚሰጉ መግለጻቸውን የኢሳት ምንጮች ካደረሱን ዘገባ ለመረዳት ተችሏል።

አቶ አብዲ ዒሌ ይቅር እንባባል በሚል በተማጽኖ ያስተላለፉበት የትላንቱ መግለጫ በተሰጠበት ዕለት በአዲስ አበባ በሶማሌ ተወላጆች የተጠራውን ስብሰባ ወኪሎቻቸውን ልከው እንዲበጠበጥ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።