የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብታቸው ተነሳ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 30/2011)የሶማሌ ክልል ምክር ቤት የ12 አባላቱን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱን አስታወቀ።

እነዚህ አባላት በክልሉ በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሌብነት ወንጀሎች እጃቸው እንዳለበት ተገልጿል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጉዳያቸውን አጣርቶ ለክስ ይፈልጋቸዋል የተባሉት 12ቱ የምክር ቤት አባላት በአብዲ ዒሌ አስተዳዳር ዘመን ከፍተኛ አመራር እንደነበሩ የሶማሌ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታውቋል።

የቀድሞ የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንትም ያለመከሰስ መብታቸው ከተነሳባቸው አመራሮች መካከል ይገኙበታል።

በሌላ በኩል የሶማሌ ክልል የቀድሞ ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ ዒሌ የተከሰሱባቸውን ወንጀሎች በሙሉ ውሸት ሲሉ ለፍርድ ቤት መግለጻቸውም ተሰምቷል

6ቱ ሀገር ቤት ናቸው። ሌሎቹ ከሀገር ወጥተዋል። ዛሬ የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ያለመከሰስ መብታችውን ያነሳባቸው የቀድሞ የአብዲ ዒሌ የካቢኔ አባላት።

በአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ሊከፈትባቸው ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑም ነው የተገለጸው።

የሶማሌ ክልል አቃቤ ህግ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት አመራሮች በሐምሌ ወር ጅጅጋ ላይ በተፈጸመውና በረካታ ሰዎች ለተገደሉበት ግጭት እጃቸው እንዳለበት ተጠርጥረው ነው።

በሌብነት ወንጀልም ይፈለጋሉ ነው ያሉት አቃቤ ህጉ።

ያለመከሰስ መብታቸው ከተነሳባቸው የምክር ቤት አባላት መካከል የቀድሞ የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ሱአድ አህመድ ፋራህ እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል።

ወይዘሮ ሱአድ ቱርክ ኢስታንቡል ከሚገኙት ባለቤታቸውና የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የግል ጣባቂ ጋር በመሆን የአሁኑን የሶማሌ ክልል አስተዳደር ለመገልበጥ ሲያሴሩ እንደነበር ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል።

ከእሳቸው በተጨማሪ አቶ መሐመድ ረሺድ ኢሳቅ፣የቀድሞ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣ አቶ መሐመድ ረሺድ ኢሳቅ የቀድሞ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣  አቶ ከደር አብዲ የሶሕዴፖ ማዕከላዊ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ አቶ አህመድ አብዲ የሶማሌ ክልል ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳድር የነበሩ ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቷል።

እነዚህ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳ ሰዎች በፌደራል ደረጃ ክስ እንደሚመሰረትባቸው የገለጹት የሶማሌ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በቁጥጥር ስር እንደሚውሉም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ የቀረበባቸውን ክስ በሙሉ ሀሰት ነው ሲሉ ለፍርድ ቤት መግለጻቸውም ተሰምቷል።

በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሌብነት ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው አቶ አብዲ ዒሌ ምንም ወንጀል አልሰራሁም፡ የፖለቲካ ክስ ነው ማለታቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።