የሲዳማ ዞን የክልላዊ መንግስት ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 23/2011) የሲዳማ ዞን የክልል መንግስት እንዲሆን የቀረበውን ጥያቄ የደቡብ ክልላዊ መንግስት በመቀበል በሁለት ሶስተኛ ድምጽ ማጽደቁ ተነገረ።

የደቡብ ክልል ምክር ቤት እያካሄደ ባለው ጉባኤ ሲዳማ በሕገመንግስቱ መሰረት ያቀረበው ጥያቄ ሕጋዊ በመሆኑ ክልላዊ የመሆን መብቱ እንዲረጋገጥ ወስኗል።

ፋይል

የሲዳማ ዞን ምክር ቤት ወደ ክልል መንግስትነት ለማደግ በሙሉ ድምጽ ይታወሳል።

የደቡብ ክልል ምክር ቤት የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄ ህገ መንግስታዊ ሂደቱን ተከትሎ እንዲፈጸም መወሰኑ ተሰምቷል።

የሲዳማ ዞን ምክር ቤት ከዚህ ቀደም የዞኑን ክልል የመሆን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መደገፉን ተከትሎ ነው ጥያቄው ለክልሉ ምክር ቤት የቀረበው።

ምክር ቤቱም በጥያቄው ላይ በዝግ ከመከረ በኋላ የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄውን ደግፎታል።

ውሳኔው ተግባራዊ ከሆነ የሐዋሳ ከተማ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል አነጋጋሪ ሆኗል።

በህገ መንግስቱ እንደተመለከተው ክልል የመሆን ጥያቄ የሚያቀርበው ብሄር፣ ብሄረሰብ ወይም ህዝብ ሊሆን ይገባል።

ይሕም በብሄር ብሄረሰብ ወይም በህዝብ ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ተቀባይነት ማግኘት እንዳለበት ነው የተደነገገው።

በዚህም መሰረት ህገመንግስቱ ላይ እንደሰፈረው ጥያቄው ለደቡብ ክልል ምክር ቤት መቅረብ ስላለበት በዛሬው እለት በይፋ መቅረቡ ነው የተገለጸው።

ከዚህ በኋላ የሚኖረውን ሂደት የክልሉ ምክር ቤት ህዝበ ውሳኔ የሚካሄድበትን ጊዜ እና ሁኔታ እንደሚወስን ተነግሯል።

ክልል የመሆን ጥያቄውም በህዝበ ውሳኔው በሚገኘው ውጤት ላይ መሰረት አድርጎ ቀጣይ ሂደቶችን እንደሚያልፍ አስታውቀዋል።