የሲናሬ ወረዳ ወጣቶች በእስር ላይ የሚገኝ አባላቸውን አሰፈቱ

የካቲት ፰ ( ስምንት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሰሜን ጎንደር ዞን በሲናሬ ወረዳ በአካባቢው ከሚካሄደው ትግል ጋር በተያያዘ አንድ የአካባቢው ወጣት መታሰሩን ተከትሎ፣ ራሳቸውን ያደራጁ ወጣቶች በምሽት ወደ እስር ቤት በመሄድ ጓዳቸውን ከማስፈታታቸውም በተጨማሪ ሌሎች እስረኞችም አምልጠዋል።
ይህንን ተከትሎ አካባቢው በወታደሮች መከበቡን የአይን እማኞች ለኢሳት ተናግረዋል። በተመሳሳይ ዜና ትናንት የነጻነት ሃይሎችን ለመምታት ወደ እንቃሽ የተንቀሳቀሰው ያገዛዙ ሰራዊት፣ ያሰበው ሳይሳካለት መቅረቱን ታጋዮች ገልጸዋል። በርካታ የሰራዊት አባላት ታጋዮቹ ወዳሉበት አካባቢ የተንቀሳቀሰ ቢሆንም፣ አስቀድመው ቦታ ይዘው ይጠባበቁ የነበሩት የነጻነት ታጋዮች ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው አካባቢውን ለቀዋል። ወታደሮች በአካባቢው ዛሬም ድረስ እንዳሉ የሚገልጹት ታጋዮች፣ እነሱ ወደአሉበት ስፍራ ደፍረው ለመምጣት እንዳልቻሉ ገልጸዋል።
ዘግይቶ በደረሰን ዜና ደግሞ በህወሃት አባላት የሚመራው ጦር ወደ ዛሪማ ተንቀሳቅሶል። ጦሩ የነጻነት ታጋዩ ጎቤ መልኬ ለማጥቃት በማሰብ ዳዊ እና አጅሬን ወደ እንቃሽ ወደሚያገናኘው ቦታ መንቀሳቀሱን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።