የሲቪክ ድርጅቶች ለሽግግር የሚረዳ የውይይት ሰነድ በጋራ ማዘጋጀታቸውን ገለጹ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 2/2010) በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚሳተፉ የተለያዩ የሲቪክ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ ለሽግግር የሚረዳ የውይይት ሰነድ በጋራ ማዘጋጀታቸውን ገለጹ።

ለፖለቲካ ሃይሎችም ጥሪ አቅርበዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ቴክሳስ ግዛት ዳላስ ከተማ መስከረም 27ና 28/2010 ለሁለት ቀናት በተካሄደው የውውይት መድረክ ላይ የተሳተፉት የሲቪክ ድርጅቶች በጉባኤው ማጠቃለያ ባወጡት ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ የኢትዮጵያ ጉዳይ አሳሳቢና ትኩረት የሚሻ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያና በአማራ እንዲሁም በደቡብ ክልል ኮንሶ በአጠቃላይ ወደ አንድ ሺ ዜጎች የተጨፈጨፉበትን አሳዛኝ ድርጊት በማስታወስ አውግዟል።

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች የሚካሄደውንም ግጭት በሀገሪቱ የተዘረጋው ብሔረሰብን መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም ውጤት ነው በማለትም አጠቃላይ ለችግሩ መፍትሔ ፍለጋ ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ አቅርቧል።

በጉባኤው ላልተሳተፉ የሲቪክ ድርጅቶችም ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ ስርአት እንዲሻገር ለሚደረገው ጥረት የሽግግሩን ሒደት የሚያግዝ የውይይት ሰነድ ማዘጋጀቱንም የማህበረሰባዊ ድርጅቶቹ ጉባኤ አስታዉቋል።

ለኢትዮጵያ ሕልውና ቀጣይነት እንዲሁም ለሉአላዊነቷ መከበር የዜጎቿ አንድነት፣የሕግ የበላይነት፣ዲሞክራሲና እኩልነት መከበርና መጠበቅ እንዳለባቸው ጉባኤው መስማማቱ ተመልክቷል።