የሱዳን ወታደራዊ ምክር ቤትና ተቃዋሚዎች ስምምነት ላይ ደረሱ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 7/2011) የሱዳን ወታደራዊ ምክር ቤትና ተቃዋሚዎች የሶስት ዓመት የሽግግር ጊዜ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገለጸ።

ከ30 ዓመታት የአልበሽር ዘመን በኋላ በወታደራዊ ምክር ቤት እየተመራች ሁለተኛ ወሯን የያዘችው ሱዳን ስልጣን በሲቪል አስተዳደር ስር እንዲሆን ከሃገር ውስጥና ከዓለም ዓቀፉ ማህብረሰብ ግፊት እየተደረገ ይገኛል።

ሰሞኑን በካርቱም እየተካሄደ ባለውና ወታደራዊው ምክር ቤት ስልጣን እንዲያስረክብ በመጠየቅ ላይ ባለውና በወታደሮች መካከል በተፈጠረ ግጭት በትንሹ 10 ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።

ቢቢሲ እንደዘገበው በዛሬው ዕለት ወታደራዊው ምክር ቤትና ተቃዋሚዎች በደረሱት ስምምነት መሰረት የሲቪል አስተዳደር በህግ አውጪው ምክር ቤት ሶስት አራተኛውን መቀመጫ ይይዛል።

ይሁንና የሀገሪቱ ትልቁ የስልጣን አካል በሆነው አስፈጻሚው ምክር ቤት ውስጥ ሁለቱም ወገኖች የበላይነት እንዲኖራቸው የሚፈልጉ በመሆኑ ገና ከስምምነት አለመድረሳቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በ24 ሰዓት ውስጥ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ወታደራዊው ምክር ቤትና የተቃዋሚዎች ጥምረት ስልጣን በመጋራት ለሶስት ዓመት የሽግግሩን ጊዜ እንደሚመሩት ቢቢሲ ዘግቧል።