የሱዳኑ ኦማር አልበሽር ከስልጣናቸው ወረዱ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 3/2011)የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር ከስልጣናቸው ተነሱ።

እሳቸውን ጨምሮ ሶስት የሱዳን ገዢ ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣናት በቁም እስር ላይ መሆናቸውን ዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ናቸው።

የ30 ዓመቱ የአልበሽር አገዛዝ ያከተመው ለወራት የዘለቀው ህዝባዊ አመጽ መቀጣጠሉን ተከትሎ ነው።

የሱዳን ጦር ቤተመንግስቱን ጨምሮ ቁልፍ ቦታዎችን መቆጣጠሩም ታውቋል።

አልበሽር ለፓርቲያቸው ምክትል የሊቀመንበርነቱን ቦታ መስጠታቸውን ቢያስታውቁም የሱዳን መንግስትን በቀጣይ የሚመራውን የሚወስኑት የጦር አዛዦች መሆናቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

የ30 ዓመቱ የአልበሽር አገዛዝ በማብቃቱ የሱዳን ህዝብ በደስታ ጎዳናዎችን ማጥለቅለቁን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የ30 ዓመቱ አገዛዝ አብቅቷል። ካርቱም ጎዳና ላይ በደስታ ሲፈነጥዙ ከነበሩ ሱዳንውያን አንዱ ለዜና ሰዎች ሲገልጽ በአልበሽር ዘመን ተወልደው ሌላ መሪ ሳያዩ ይህቺን ምድር በሞት የተሰናበቱ ሰዎች ይሄን ቀን ቢያዩ ምንኛ ደስ ባላቸው ሲል ገልጿል።

የሱዳን ከተሞች ዛሬ በፈንጠዚያ ተጥለቅልቀዋል። ህዝቡ አደባባይ ወጥቶ የ30 ዓመቱን ዘመን ማብቃት እያበሰረ ነው።

በእርግጥም በአፍሪካ ለረጅም ዓመታት ስልጣን ላይ በመቆየት አንዱ የሆኑት አልበሽር ዛሬ ከስልጣናቸው መወገዳቸው የዓለም መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ወስዷል።

ለስድስት ወራት ያህል በህዝባዊ ተቃውሞ ወንበራቸው ሲነቀነቅ የከረመባቸው ኦማር ሀሰን አልበሽር በወታደራዊ ሃይል ተገፍተው ስልጣናቸውን እንዲለቁ መደረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ዘግይተው የሚወጡ ዘገባዎች አልበሽር ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት እንደተረገባቸው የሚያረጋግጡ ናቸው።

የጦሩ ክፍል ሃገሪቱን በቁጥጥሩ ስር ማድረጉን ተከትሎ ሱዳን በወታደራዊ አገዛዝ እጅ ላይ እንዳትወድቅ ስጋቱ ከወዲህ እየተገለጸ ነው።

ጦሩ የሱዳንን ብሔራዊ ቴሌቪዥንን ጨምሮ ቁልፍ የደህንነትና የጸጥታ ህንጻዎችን መቆጣጠሩም ተገልጿል።

የፖለቲካ እስረኞችን በሙሉ ከእስር ነጻ ማድረጉ ያሳወቀው ጦሩ ህግና ስርዓት በማስከበር ላይ መሆኑን አስታውቋል።

የመከላከያ ሚኒስትር አዋድ መሃመድ አህመድ በቴሌቪዥን ቀርበው የሁለት ዓመት የሽግግር መንግስት መቋቋሙንና ወታደራዊ ምክር ቤት ሃገሪቱን በጊዜያዊነት እንደሚመራት አስታውቀዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ መግለጫ የሱዳናውያንን ደስታ ከግማሽ ቀን እንዳይዘልቅ ማድረጉን ነው ሲ ኤን ኤን ማምሻውን የዘገበው።

ስልጣን ለሲቪል አስተዳደር እንዲሰጥ የሚጠይቅ የተቃውሞ ትዕይንት ምሽት ላይ በካርቱም የወታደራዊው ዋና ማዘዣ መስሪያ ቤት ፊት ለፊት በመካሄድ ላይ መሆኑ ታውቋል።

የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ስጋት በተጠናከረበት በዛሬው ዕለት ሱዳን ተመልሳ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን በሚይዙ ወታደሮች እጅ መውደቋ አሳሳቢ ሆኗል እየተባለ ነው።

በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዙት አልበሽር እሳቸውንም ፈንቅሎ ስልጣን በጊዜያዊነት በያዘው የሱዳን ጦር ዳግም የጭቆና ዘመን እንዳይከሰት ሱዳናውያን ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።

በዚህም ተባለ በዚያ የ30 ዓመት የአልበሽር ዘመን ፍጻሜው ሆኗል።

በቁም እስር ላይ መሆናቸውን የሚገልጹ ዘገባዎች አልበሽር ቤተመንግስት ውስጥ በአንድ ክፍል ውስጥ እንደሚገኙ አትተዋል።

ሁኔታዎች እየተቀያየሩባት ባለው ሱዳን ደስታና ስጋት ያንዣበበት የመጀመሪያ ቀን ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል።