የሰራዊቱ አባላት ከትግራይ እንዳይንቀሳቀሱ መደረጉ ተገቢ አይደለም ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 01/2011) የመከላከያ ሰራዊት ተሽከርካሪዎችና የሰራዊቱ አባላት ከትግራይ እንዳይንቀሳቀሱ መደረጉ ተገቢ አይደለም ሲሉ ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ገለጹ።

በማንኛውም መልኩ ግጭትና ጦርነት የሚቀሰቅስን ተግባር አንቀበልም ያሉት የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የህዝቡን ስጋት ብንረዳም የጦር መሳሪያዎቹ የፌደራሉ መንግስት ንብረት በመሆናቸው የመሳሪያውንና የሰራዊቱን ስምሪት የምንወስነው እኛ ሳንሆን የፌደራሉ መንግስት ነው ብለዋል።

በትግራይ ህዝብ ሽፋን አድርገው ትርምስ ለመፍጠር የሚሞክሩ ወገኖች መኖራቸውን ገልጸዋል።

“በጦር መሳሪያ አንተማመንም አስፈላጊ ከሆነ ከዚህም በላይ የሆነ የጦር መሳሪያ ማምጣት እንችላለን” ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚያስፈልገን የጦር መሳሪያ ሳይሆን ሰላምና ልማት ነው ብለዋል።

“ሰራዊቱ የኢትዮጵያም የትግራይም ነው” ያሉት የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር “የፌደራሉ መንግስት ስጋት የለብንም ቢልም” የትግራይ ህዝብ ግን ስጋት አለው።

የትግራይ ህዝብ ግን ስጋት አለኝ ብሎ ሰራዊቱን አያግትም፣ ህዝቡን ሽፋን አድርጎ ትርምስ ለመፍጠር የሚሞክር ሃይል አለ፣ እነርሱም ጥቂቶቹ ናቸው እርግጠኛ ነኝ ይጋለጣሉ” ሲሉም መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ከኤርትራ በኩል የሚመጣ ስጋት ባለመኖሩ ሰራዊቱን ከዚያ ለማንሳት ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

በጉዳዩ ላይ ከትግራይ ክልል መንግስት ጋርም ውይይት መደረጉን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እንዳይንቀሳቀሱ ሲታገዱ ትናንት ለሁለተኛ ግዜ ሲሆን በዚህም 25 ከባድ ተሽከርካሪዎችና 5 መለስተኛ ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ ተደርገዋል።

ማን እንዳሰማራቸው ያልታወቀ ወጣቶች ተሽከርካሪዎቹ ላይ ዘለው በመውጣትና መንገድ ላይ በመተኛት ጉዞውን ገተዋል።

እነዚህ ሃይሎች መከላከያ ሰራዊቱ እንዳይወጣ መንገድ እየዘጉ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ ታይተዋል።

በሳምንቱ መጀመሪያ የሁመራ ኢምሃጅር መንገድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በተገኙበት ሲከፈት የተደራጁ ሃይሎች ተቃውሞ ሲያሰሙ ታይተዋል።

እነዚህ የተደራጁ እንቅስቃሴዎች ህዉሃት እንደ ቡድን ያደረጃቸው ወይንም የሆነ አንጃ ያሰማራቸው የታወቀ ነገር የለም።

ሆኖም አላማው የመከላከያ ሰራዊቱ ርምጃ እንዲወስድና የሰዎችን ቁስልና አስከሬን እያሳዩ የትግራይን ህዝብ ለማነሳሳት ያለመ መሆኑን ሂደቱን የገመገሙ የፖለቲካ ምሁራን ይገልጻሉ።