የሞዛምቢክ ከፍተኛ ባለስልጣናት ተከሰሱ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 01/2011)በሞዛምቢክ በብድር የተገኘ የሃገር ሃብትን ያጭበረበሩ ከፍተኛ ባለስልጣናት ተከሰሱ።

የሃገሪቱ የቀድሞ የገንዘብ ሚኒስትርን ጨምሮ በአጠቃላይ 18 ያህል ሰዎች በብድር በተገኘ 2 ቢሊዮን ዶላር ላይ የማጭበርበር ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ሲከሰሱ ሁለት ዓለም አቀፍ ባንኮችም ተባባሪ ሆነው መገኘታቸውም ተመልክቷል።

የሞዛምቢክ መንግስት በባለስልጣናቱ ላይ የማጭበርበር ወንጀል ክስ የመሰረተው የክሬዲት ስዊዝ ባንክ የቀድሞ ሶስት ሰራተኞች ለንደን ላይ በወንጀሉ ተጠርጥረው መታሰራቸውን ተከትሎ ነው።

በዚህ ወንጀል የተጠረጠሩት የሞዛምቢክ የቀድሞ የገንዘብ ሚኒስትር ማኑኤል ቻንግ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ሌሎች የወንጀሉ ተባባሪዎች ኒዮርክ ላይ ተይዘዋል።

በከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ የምትገኘው ሞዛምቢክ የገንዘብ ሚኒስትር የነበሩት የ63 ዓመቱ ማኑኤል ቻንግ በማጭበርበሩ ሂደት ዋነኛ ተዋናይ መሆናቸው ተመልክቷል።