የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ እድገት ዜና ባዶ ፕሮፓጋንዳ ነው ሲሉ አጣጣሉት

ሰኔ ፱ ( ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ የተለያዩ ኢኮሚስቶችን በማናገር እንደዘገበው ኢትዮጵያ በማንፋክቸሪንግ ዘረፍ ከፍተኛ እድገት እንዳገኘች ተደርጎ የሚቀርበው ዘገባ ባዶ ፕሮፓጋንዳ ነው ብሎአል። ኢትዮጵያ እንኳንስ አፍሪካ ምሳሌ ልትሆን በማንፋክቸሪንግ ዘረፍ፣ ከአፍሪካ አገራት ያነሰ ስራ መስራቱዋን ጋዜጣው ዘግቧል። የኢትዮጵያ መንግስት የተሳካላት ነገር ቢኖር፣ አገሪቱ በኢንዱስትሪው ዘርፍ እያደገች ነው የሚለውን ፕሮፓጋንዳ ተቀባይነት እንዲያገኝ በማድረግ በኩል ነው በማለት ኢኮሚስቶች ተናግረዋል።
የማንፋክቸሪንጉ ዘርፍ ለአጠቃላይ ኢኮኖሚው የሚያደርገው አስተዋጽኦ በደርግ ዘመን ከነበረው ጋር ሲነጻጸር እንኳ እያሽቆለቆለ መሄዱን የሚገልጸው ጋዜጣው፤ በፈረንጆች አቆጣጠር በ2015 በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ውስጥ የማኑፋክቸሪንግ ድርሻ 4. 1 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በ1997 ከነበረው 7.8 በመቶ ጋር ሲነጻጸር እያሽቆለቆ መሄዱን ያሳያል ብሎአል።
ከየትኛውም የአፍሪካ አገር ጋር ሲነጻጸር፣ በኢትዮጵያ የእንዱስትሪ እድገቱ ዝቅተኛ ነው። ሳውዝ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ አይቮሪኮስት፣ ካሜሩን፣ ቤኒን፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክና ዝምባብዌ ማንፋክቸሪንግ 10 በመቶ የሚሆነውን የአኮኖሚ ድርሻ ሲይዝ በዩጋንዳና ናይጀሪያም ተቀራራቢ ቦታ ይይዛል።
ኢትዮጵያ ለምን የአፍሪካ የኢንዱስትሪ እድገት ሞዴል ተደርጋ ትቀርባለች በማለት የሚጠይቀው ጋዜጣው፣ የተለያዩ ኢኮኖሚስቶች የሰጡትም መልስ አካቷል። ሪናይሰንስ ካፒታል በሚባል ተቀማጭነቱ ሞስኮ በሆነ የኢንቨስትመንት ባንክ ውስጥ የሚሰሩት ኢኮኖሚስቱ ቻርለስ ሮበርትሰን፣ “ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቀተኛ የማንፋክቸሪንግ እድገት ማሳየቷ ትክክል ቢሆንም፣ ብልጠት የተሞላበት የህዝብ ግንኙነት ስራ በመስራት በመሬት ላይ የሌለውን እድገት እንዳለ አድርጋ ለማቅረብ ችላለች” ብለዋል።
ካፒታል ኢኮኖሚክስ በሚባል ተቋም ውስጥ በአማካሪነት የሚያገለግሉት ኢኮሚስቱ ጆን አሽባውርነ በበኩላቸው፣ “ ሚዲያው ኢትዮጵያን የማንፋከቸሪንግ እድገት አጋኖ ያቀርበዋል። በቅርበት ካየኸው አዲስ አበባ ያሉት ባለስልጣናት ባይቀበሉትም፣ የማንፋክቸሪንግ እድገታቸው ከአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው።” ሲሉ አስረድተዋል።
ውዳሴው ቢኖርም፣ ኢትዮጵያ በ2015 44 ሚሊዮን የሚያወጡ የጫማ ምርቶችን ለአለም ገበያ ማቅረቡዋ፣ ይህም አሃዝ ከቬትናም ጋር ሲነጻጸር፣ 0.25 በመቶ እንደሚያክል ጋዜጣው ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ስም የሚነሳውና ትልቁ ስኬት ተደርጎ የሚጠራው ምናልባትም ታላላቅ ስም ያላቸውን ኩባንያዎች ወደ አገሯ ለማስገባት መቻሉዋ ነው የሚሉት ሚ/ር አሽቦርን፣ ከአንዳንድ አፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸሩ እነዚህ ኩባንያዎች የሚያመርቱት ምርት የጥራት ደረጃ የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ ለስሟ መነሳት አስተዋጽኦ ሳያደርግ እንዳልቀረም ግምታቸውን ገልጸዋል።
ሚ/ር ሮበርትሰን በበኩላቸው ከቻይና ጋር የመሰረተችው የኢኮኖሚ ግንኙነትና የቻይናን የኢኮኖሚ ሞዴል ለመከተል መፍቀዷ ስሟ አብሮ እንዲነሳ ሳያደርገው እንዳልቀረ ይገልጻሉ።አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ኢኮኖሚያቸው የሚመራው በግል ባለሃብቶች ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ግን እንደ ቻይና ኢኮኖሚው ከላይ ወደ ታች እንደሚመራ ይናገራሉ። “ ህዝቡ ቻይና ላለፉት 30 አመታት ፈጣን የኢኮሚ እድገት አሳየች፣ ኢትዮጵያም ለ10 አመታት 11 በመቶ እድገት አሳየች ፣ የቻይናን እግር ተከትላ ኢንዱስትሪዋን እያሳደገች ነው በማለት ይናገራሉ። ይህ ግን ትክክል አይደለም” ሲሉ ኢኮኖሚስቱ ያክላሉ።
ናይጀሪያን የመሳሰሉ አገራት የኢትዮጵያን አካሄድ ሊከተሉ አይችሉም የሚሉት ኢኮኖሚስቱ፣ ምክንያታቸውን ሲያብራሩም “ በቅድሚያ ኢትዮጵያ፣ በሌሎች የአፍሪካ አገራት የሌለ ለዘመናት የቆየ ጠንካራ ቢሮክራሲ አላት፣ አገሪቱ ለረጅም ዘመናት ማለትም ከ12 70 ጀምሮ ጥንታዊ መንግስት ያላት አገር ናት። ሁለተኛ ናይጀሪያ ከኢትዮጵያ በበለጠ ሃብታም አገር ናት፣ በዚህም የተነሳ የናይጀሪያ ህዝብ በተሻለ ነጻነት መኖር ለምዷል። ናይጀሪያዎች በጣም ዲሞክራቶች ናቸው። በጣም ነጻ ናቸው። ሃሳባቸውን በነጻነት የሚገልጹ ህዝቦች ናቸው። የኢትዮጵያ መንግስት ለ30 አመታት የቆየ ነው። ዘቅተኛ ሙስና ቢኖርም፣ በኢትዮጵያ ማንም ምንም የለውም። ናይጀሪያውያን ከኢትዮጵያውያን በ3 እጥፍ ባለጸጋ ናቸው። ይህን ህዝብ እንደ ኢትዮጵያ ህዝብ በኮሚኒስት ሳጥን ውስጥ ላስገባው ብትለው እሽ አይልም። ጋና፣ ሴኔጋልና ኬንያ፣ ይህን ሂደት አልፈው ከተራመዱ ቆይተዋል።” በማለት የኢህአዴግን የፖለቲካ ኢኮኖሚ መርሆ አጣጥለዋል።
ለወትሮው በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የተሻለ ዘገባ ያቀርብ የነበረው ፋይናንሻል ታይምስ፣ እንዲህ አይነት ርእስ መርጦ ዘገባ ማቅረቡ ምናልባትም በቅርብ ጊዜ በአገሪቱ የተነሳው ህዝባዊ አመጽ መነሻ ሳይሆነው አየቀርም። ጋዜጣው ኢትዮጵያ እያደገች ነው ከተባለ ለምን ህዝባዊ አመጽ ሊነሳ ቻለ በማለት ቀድም ሲል ባወጣው አንድ ዘገባው ጥያቄ አቅርቦ ነበር። በቅርቡ በኦሮምያና አማራ የታው ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ በኢኮኖሚው ላይ ብቻ ሳይሆን በአገዛዙ የ26 አመታት አለማቀፍ ገጽታ ላይም አሉታዊ ተጽኖው እያመጣ መሆኑ እየታየ ነው።