የሜቴክ ዳይሬክተር የስራ መልቀቂያ አቀረቡ

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 17/2011) አወዛጋቢው የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሜቴክ ዳይሬክተር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተሾሙት ዶክተር በቀለ ቡላዶ የስራ መልቀቂያ አቀረቡ።

ምክትል ዳይሬክተሩ ብርጋዴር ጄኔራል አህመድ ሃምዛ በምትካቸው መሾማቸውም ተመልክቷል።

ሜቴክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበደረው ገንዘብ16 ቢሊየን ብር መድረሱም ተገልጿል።

የባንኮችን ሕጋዊ አሰራር በመጣስ አለም አቀፍ ግዢዎችን ያለጨረታ እንዲያከናውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተባባሪ ሆኖ መቆየቱንና ብሔራዊ ባንክም በዝምታ መመልከቱን መረዳት ተችሏል።

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በእንግሊዘኛው ምህጻረ ቃል ሜቴክ በድረገጹ እሴቶቻችን ሲል ያስቀመጠው”ለሕዝባችን፣ለመንግስታችን እንዲሁም ለደንበኞቻችንና ለቃላችን ታማኝ ነኝ”የሚል ነው።

በተግባር ግን ሜቴክ ቃል በገባው መሰረት በሁለት አመትና በአመት ከመንፈቅ አስረክባለሁ ያላቸውን የስኳር ፋብሪካዎችና ሌሎች ግንባታዎች በቃሉ መሰረት መፈጸም ባለመቻሉ ከፍተኛ ወቀሳ ቀርቦበታል።

ከፍተኛ የሃገር ሃብት በማካሄድ በመንግስት በይፋ የተወነጀለው፣መሪዎቹንም ለወህኒ አሳልፎ የሰጠው በጠቅላላው ለደንበኞቹም፣ለመንግስትም ሆነ ለሕዝብ ታማኝ መሆን የተሳነው ሜቴክ በ7 ወራት ጊዜ ውስጥ 2ኛውን ዳይሬክተር ቀይሯል።

በአዋጅ ከተቋቋመበት ከ2002 ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 2010 በብቸኝነት በዋና ዳይሬክተርነት የቆዩት ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው ዛሬ በከባድ ሌብነት ተጠርጥረው ወህኒ መሆናቸው ይታወቃል።

ወደ ወህኒ ከመጋዛቸው በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መመጣታቸው ተከትሎ በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ለቀቁ ተብሎ ከሚያዚያ 2010 ጀምሮ መቀሌ ውስጥ ቆይተዋል።

የሜቴክ የዘርፉ ፋይል ሲገለጥና የርሳቸው ምክትላቸው ሌሎች ሃላፊዎች እንዲሁም ደጋፊዎችና የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ጭምር ሲታሰሩ ወደ ሱዳን ሲሸሹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው ከ7 ወራት በፊት በዶክተር በቀለ ቡላዶ የተተኩ ቢሆንም ዶክተር በቀለ ከወር በፊት በፈቃዳቸው የስልጣን መልቀቂያ ማቅረባቸው ታውቋል።

ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ መልቀቂያ ባቀረቡት ዶክተር በቀለ ቡላዶ ምትክ ምክትል ሆነው ሲሰሩ የቆዩት ብርጋዴር ጄኔራል አህመድ ሃምዛ መሾማቸውን አዲስ ፎርቹን በዘገባው አስፍሯል።

20ሺ ያህል ሰራተኞችን ይዞ በ10 ቢሊየን ብር ካፒታል በዋናነት በደርግ ዘመን የተቋቋሙትን የመከላከያ ኢንደስትሪዎችን በማቀናጀት የተዋቀረው ሜቴክ በሃገሪቱ ውስጥ ሲያካሂደው ከቆየው ዘረፋ ጋር በተያያዘ የሃገሪቱ ባንኮች በጥቅምና በፍራቻ ተባባሪ መሆናቸውንም የቅርብ ምንጮች ይገልጻሉ።

ከ1 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚፈጸም ማናቸውም ግዢ አለም አቀፍ ጨረታ መውጣት እንዳለበት በሃገሪቱ በግልጽ በህግ ቢቀመጥም ሜቴክ ይህንን የሃገሪቱን ሕግ ተላልፎ የበርካታ ሚሊየን ዶላር ግዢ ያለ ጨረታ ሲያከናውን መቆየቱ ተመልክቷል።

ያለ ጨረታ እቃዎችን በ400 ፐርሰንት እጥፍ ሲገዛ ባንኮቹ ሒደቱን በማመቻቸት ተባባሪ መሆናቸውንም የቅርብ ምንጮች ይገልጻሉ።

አለም አቀፍ ግዢዎች የሚፈጸሙት ሌተር ኦፍ ክሬዲት በባንክ በኩል በመክፈት እንደሆነ የሚገልጹት ባለሙያዎች የሜቴክ ግዢ የቀረበለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1 ሚሊየንና ከአንድ ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ግዢ ከመፍቀዱ በፊት የጨረታ ሰነዱን ማየትና ማረጋገጥ ይጠበቅባታል።

የጨረታውን ሒደት ለብሔራዊ ባንክ ማሳወቅ ግዴታው ቢሆንም ሁለቱም ባልተሟሉበት ደካማው የሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪ በሜቴክ ሲበዘበዝ መቆየቱ ተመልክቷል።

ሜቴክ ከ2002 ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ የተደራጀ ዘረፋ ሲያደርግ ቆይቷል የሚሉት እነዚህ ወገኖች ከተለያዩ ተቋማትና ድርጅቶች ከባከነው የሃገር ሃብት በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወሰደው እዳ ብቻ 16 ቢሊየን ብር መድረሱም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድሩን ለመልቀቅ የአዋጭነት ጥናት ወይንም ፊዚቢሊቲ ስተዲ መመርመር ቢኖርበትም ይህን ሳይሆን በመቅረቱ ለከሰሩ ፕሮጀክቶች 16 ቢሊየን ብር ወጪ መሆኑ ተገልጿል።