የሜቴክ ሃላፊዎች በፈጸሙት ዝርፊያ ላይ ምርመራው እንደቀጠለ ነው

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 1/2011) የመሰረታዊ ብረታብረት ኮርፖሬሽን ሜቴክ ሃላፊዎች በሃገሪቱ ሃብት ላይ በተለይም በሕዳሴው ግድብ ያካሄዱትን የተደራጀ ዘረፋ በተመለከተ ምርመራ መቀጠሉ ታወቀ።

በዘረፋው ሒደት ተዋናይ የሆኑ የሌሎች ተጨማሪ ደላሎችና ግብረ አበሮች ዝርዝር መውጣት ጀመሯል።

የሜቴክ ሃላፊዎች በዘር ተደራጅተው በሃገሪቱ ሃብት ላይ በሚያደርጉት የተደራጀ ዘረፋ በደላላነት የተሳተፉና በዝርፊያው ተባባሪ የነበሩ ግለሰቦች ዝርዝር በመውጣት ላይ ይገኛል።

በድሬደዋ ከተማ የባለ ኮከብ ሆቴል ባለቤትና የመከላከያ ትራንስፖርት ክፍል ሃላፊ ኮለኔል ወዲ ቀሺ፣የጄኔል ክንፈ ዘመድ የሆኑት ወይዘሮ ለምለም እንዲሁም ሃይሌ ላምባ የተባሉ ግለሰቦች ከሜቴክ ሃላፊዎች ጋር በትትብር እንደሚሰሩ ተመልክቷል።

ሃይሌ ላምባ የተባሉት ለህዳሴው ግድብ ነዳጅ የሚያቀርቡ ሲሆን የሕወሃት ንብረት የሆነው ትራንስ ኢትዮጵያ የትራንስፖርት ዘርፉን ተቆጣጥሯል።

ሌላው የሕወሃት ንብረት የሆነው መሶቦ የሲሚንቶ ማቅረቡን ስራ ሲወስድ መስፍን ኢንጂነሪንግ የተባለው የሕወሃት ኩባንያ ደግሞ የብረታ ብረት ስራዎችን እንደሚሰራም ተመልክቷል።

ይህንን በዘርና በፓርቲ የሚካሄድ የተደራጀ ዘረፋ የተቃወሙ ከፍተኛ እንዲሁም መስመራዊ መኮንኖችና ተራ ወታደሮች ከድርጅቱ ተባረዋል።

ሌሎች ደግሞ ውስጥ ሆነው የተደራጀውን የዘረፋ ተግባር በተለያየ መንገድ ሲያጋልጡ መቆየታቸውን የቅርብ ምንጮች ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በሜቴክ አማካኝነት የሚደረገው ዘረፋ መቆሙን የሚገልጹት ምንጮች፣የሜቴክ ሃላፊዎች ከሚዘርፉት ሃብት ድጎማ ሲያደርጉለት የነበረው የደደቢት እግር ኳስ ቡድን ድጋፉ ስለቆመበት መቀመጫውን ከአዲስ ወደ መቀሌ አሻግሯል።

የደደቢት ቡድን በሜቴክና በመከላከያ በሚደረግለት ድጋፍ የቡድኑ አባላት በአዲስ አበባ በሆቴል ውስጥ ይኖሩ እንደነበርም ተመልቷል።

ሜቴክም ሆነ መከላከያ ለደደቢት እግር ኳስ ቡድን ድጋፍ የሚያደርጉበት ሕጋዊና መዋቅራዊ ግንኙነት እንደሌላቸውም ታውቋል።

ሜቴክ ውስጥ በሚካሄደው ዘረፋ በድለላው መስክ ተሳታፊ በመሆን ከፍተኛ የሃገር ሃብት በመመዝበር ተሳታፊ የሆኑትን ብርጋዴር ጄኔራል መላኩ ሽፈራው ሰሞኑን በኢሳት ላይ ማጋለጣቸው ይታወሳል።

ኮለኔል ተወልደ፣ከለኔል ክብሮም፣ኮለኔል ግደይ ፎሮ፣አቶ ሽመልስ ክንዴ፣አቶ ደግነህና አቶ አትክልቲ የተባሉት ዋና ተዋናዮችና በዘረፋው በተባባሪነት የከበሩ መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።