የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከዱ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 15/2010)ከሞያሌ በሳምንቱ መጀመሪያ የተሰወሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት መክዳታቸውን ምንጮች ለኢሳት አረጋገጡ።

የከዱት የሰራዊቱ አባላት ቁጥርም 38 እንደሆነ ምንጮቹ ገልጸዋል።

እነሱን ለመፈለግ የወጣው ሃይልም አለመመለሱ ታውቋል።

ሆኖም ለአሰሳ በወጣው ሃይል ውስጥ በተፈጠረ ውዝግብ አንድ ወታደር ሲገደል አንድ መቁሰሉን ምንጮቹ ተናግረዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመባቸው የኦሮሞ ተወላጅ ወታደሮች መሆናቸውም ተመልክቷል።

በሳምንቱ መጀመሪያ ከሞያሌ ተነስተው ለአሰሳ የወጡት ወታደሮች ከ24 ሰአታት በላይ መሰወራቸውን ተከትሎ እነሱን የሚፈልግ አሳሽ ቡድን በቀጣዩ ቀን ተከትሎ ነበር።

ይህ ሃይል የጠፉትን ወታደሮች ዱካ ሳያገኝ ሁለት ቀናት ያህል ከማሰነ በኋላ የቀደሙት ሆን ብለው መክዳታቸው ተረጋግጧል።- በዛታቸውም 38 መሆኑ ታውቋል።

የጠፉትን ፍለጋ በወጡት ወታደሮች ውስጥ በተፈጠረ ግጭትም አንድ ወታደር ሲገደል ሌላ አንድ መቁሰሉም ታውቋል።

ለዚህም መነሻ የሆነው ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ በተዘረጋው የኤሌክትሪክ መስመር ላይ ጥቃት ሰንዝራችኋል በሚል የቃኚው ቡድን ሃላፊ በሁለት የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ጥቃት በመሰንዘራቸው እንደሆነም ተመልክቷል።

ትክክለኛ ስማቸው ያልተገለጸውና በቅጽል ስማቸው ጌዶ በተባሉት የሕወሃት ታጋይ ትዕዛዝ አንድ የኦሮሞ ተወላጅ ወታደር ሲገደል ሌላ የኦሮሞ ተወላጅ መቁሰሉም ታውቋል።

በዚህም የእርስ በርስ ተኩስ መነሳቱ የተገለጸ ሲሆን ተጨማሪ ጉዳት ስለመድረሱ ማረጋገጥ አልተቻለም።

ከከዱት ወታደሮች ጋር በተያያዘ ግንኙነት አለህ በሚል አንድ የሬዲዮ መገናኛ ሰራተኛ መታሩን መዘገባችን ይታወሳል።

በጥቃቱ አነስተኛ ጉዳት የደረሰበት የኤሌክትሪክ መስመርም መጠገኑ ታውቋል።