የመቱ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አድማ በማድረግ ላይ ናቸው

የመቱ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አድማ በማድረግ ላይ ናቸው
(ኢሳት ዜና ግንቦት 08 ቀን 2010 ዓ/ም) ተማሪዎቹ አድማውን የጀመሩት ከጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ ተፈናቅለው በመቱ ዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የተደረጉት ተማሪዎች ወደ ጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ ተመልሰው ትምህርታቸውን እንዲጨርሱ መወሰኑን ተከትሎ ነው። ተማሪዎቹ አስተማማኝ ሰላም በሌለበትና ለህይወታችን ዋስትና በማናገኝበት ሁኔታ ወደ ጅግጅጋ ለመመለስ አንችልም በማለት በማለት ለዩኒቨርስቲው ባለስልጣናት ቢያሳውቁም፣ ባለስልጣናቱ ግን የተማሪዎችን ጥያቄ የሚቀበሉት አልሆነም። በዚህም ተነሳ ዛሬ ሁሉም የግቢው ተማሪዎች የትምህርት ማቆም አድማና ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን፣ ፈደራል ፖሊሶች ወደ ግቢ በመግባት በተማሪዎች ላይ ድብደባ አካሄደዋል። አንድ ተማሪ ግንባሩ ላይ በጽኑ ቆስሎ ሆስፒታል ገብቷል። በርካታ ተማሪዎች መጠነኛ ጉዳት እንደደደረሰባቸው የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
ከጅጅጋ ዩኒቨርስቲ ለቀው በሃረማያ ዩኒቨርስቲ ተመድበው ትምህርታቸውን የጨረሱ ተማሪዎች የትምህርት ማስረጃቸውን ሲጠይቁ ጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ ሄደው እንዲጠይቁ ሃረማያ ዩኒቨርስቲ መልስ የሰጠ ሲሆን፣ ምሩቃኑ ወደ ጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ ሄደው ሲጠይቁ ደግሞ ዩኒቨርስቲው አላውቃችሁም በሚል ሸኝቷቸዋል። በመሃሉ ተማሪዎች የትምህርት ማስረጃቸውን ለማግኘት መቸገራቸውን የሰሙ የመቱ ተማሪዎች፣ ነገ እነሱም ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ተመሳሳይ ችግር ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ይናገራሉ።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች ከኢትዮ-ሶማሊ ክልል ሲፈናቀሉ በጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ ሲማሩ የነበሩ የኦሮሞ ተማሪዎች ለደህንነታቸው በመስጋት በኦሮምያ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች እንዲመደቡ በጠየቁት መሰረት ትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎችን በሃረማያና መቱ ዩኒቨርስቲዎች መድቧቸው ነበር። በሶማሊ ክልል ያለው ጸጥታ ባልተሻሻለበት ሁኔታ ተማሪዎች ወደ ጅግጅጋ እንዲመለሱ መጠየቃቸው ትክክል አለመሆኑን የሚጠቅሱት ተማሪዎች፣ ትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔውን እንደገና እንዲያጤነው ጠይቀዋል።
ሁሉም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም ከጅግጅጋ ለተፈናቀሉ ጓደኞቻቸው ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት አብረዋቸው ትምህርት ማቆማቸውን ተማሪዎቹ ተናግረዋል።