የመስቀል በዓል በመላው ኢትዮጵያ በሰላም ተከብሮ ዋለ።

የመስቀል በዓል በመላው ኢትዮጵያ በሰላም ተከብሮ ዋለ።
( ኢሳት ዜና መስከረም 17 ቀን 2011 ዓ/ም ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ የሚከበረው የደመራ እና የመስቀል በዓል በመላ ኢትዮጵያ በድምቀት ተከብሯል። ምእመናኑ ሃይማኖታዊ ስርዓትና ትውፊታቸውን ጠብቀው የሚያከበሩትን የመስቀል በዓል አስመልክቶ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ ለእምነቱ ተከታዮች መልዕክት አስተላልፈዋል።
”ይህ ታላቅ እና ግሩም በዓል በዓልነቱ የክርስትያን ወገኖቻችን ቢሆንም ቅሉ ክብሩ እና ሃብትነቱ ግን የመላ ኢትዮጵያውያን ጸጋ ነው፡፡ በአለ መስቀል ከሃይማኖታዊ አስተምህሮቱ እና ከመንፈሳዊ እውነትነቱም ባሻገር የሚያስተምረን እና በውል እንድናስተውል የሚያስገድደን ሌላም ቁም ነገር ነገር አለው፡፡
እውነት የቱንም ያህል ዘመን፣ በምንም ያህል ውሸትና ቅጥፈት፣ ተንኮልና ሤራ፣ በየትኛውም ስልጣን እና ክፋት ብትሸፈንም በዘላቂነት ልትቀበር እንደማትችል አይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ ለጥቂት ጊዜ ፀሐይን እንደሚሸፍን ደመና እውነትን ለተወሰነ ጊዜ መከለል፣ ውሸትንም እውነት ማስመሰል ይቻል ይሆናል፡፡ በመጨረሻ ግን እውነት እንደምታሸንፍና ከተቀበረችበትም ወጥታ ቀባሪዎቿን እንደምታሳፍር ለማስረዳት የክርስቶስ መስቀል ታሪክ ግሩም ማስረገጫ ነው፡፡” ብለዋል።
በተጨማሪም የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን ጳጳስ ብጹዕ ወ ቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የሞተር ዊልቸር ስጦታ ማበርከታቸውን የጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ቃል አቀባይ አቶ ፍሱም አረጋ አስታውቀዋል።
ብጹዕ ወ ቅዱስ አቡነ ማትያስ በበኩላቸው ”መስቀሉ ላይ ያለው አስተምህሮ እየተበደሉ ይቅርታ ማድረግ ነው።” በማለት ሁሉም ዜጋ ለምኅረትና ለእርቅ እራሱን እንዲያዘጋጅ መለዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በዓሉ በመዲናችን አዲስ አበባ ጨምሮ በጎንደር፣ አሰላ፣ ሃረር፣ ደሴ፣ አዲግራት፣ ጂማ፣ አዋሳ፣ ሶዶ፣ ጂጂጋን በመሳሰሉ ታላላቅ ከተሞች በድምቀት ተከብርዋል። እስካሁንም ከደመራው ጀምሮ ቀን ጀምሮ ምንም ዓይነት የጸጥታ ችግር አልተፈጠረም።