የሕዳሴው ግድብ ገንዘብ የገባበት አይታወቅም ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 30/2010)ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ ተሰብስቦ ከነበረው ገንዘብ ውስጥ ከግማሽ በመቶ በላይ የሚሆነው የገባበት አይታወቅም ተባለ።

ገንዘቡ የደረሰበትን ለማወቅም በመጣራት ላይ መሆኑን የሜቴክ የኮሜርሻልና ሲቪል ምርቶች ኦፕሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ገልጸዋል።

በ5 አመት ይጠናቀቃል የተባለው የህዳሴው ግድብ ግንባታም ቢሆን ከ25ና ከ30 በመቶ በላይ አለመጠናቀቁም ታውቋል።

አቃቤ ህግ በበኩሉ በዚህ ሒደት ውስጥ ያሉ አካላት በሙሉ ተጠያቂ ይሆናሉ ብሏል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ባለቤትነት እንዲሁም በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን(ሜቴክ) እና ሳሊኒ ኩባንያ የስራ ተቋራጭ የሆኑበት የሕዳሴው ግድብ አፈጻጸም ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ብክነትና ምዝበራ የተፈጸመበት መሆኑ ተገለጸ።

“ሕዳሴ ሲገለጥ” በሚል ርዕስ ዋልታ ኢንፎርሜስን ማዕከል ባዘጋጀው የምርመራ ዘገባ የሕዳሴው ግድብ በሰባት አመት ውስጥ ያለበት አፈጻጸም ያለበት ደረጃ ከ25 እስከ 30 በመቶ ብቻ መሆኑን አመላክቷል።

በተለይም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራውን የተረከበው የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን(ሜቴክ) ያለጨረታ ፕሮጀክቱን አጠናቆ ለማስረከብ በ25 ነጥብ 58 ቢሊየን ብር ተዋውሎ ስራውን መጀመሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ዶክተር አብርሃም በላይ ገልጸዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚው አክለው እንደገለጹት ኮርፖሬሽኑ እስከ አሁን ድረስ ወደ 16 ነጥብ 79 ቢሊየን ብር ክፍያ ተፍጽሞለታል።

ይህ ክፍያ ከፕሮጀክቱ አጠቃላይ ክፍያ 65 በመቶ ይሸፍናል።

በሌላ በኩል የሜቴክ የስራ አፈጻጸም 42 በመቶ ያህል ብቻ መሆኑን ዶክተር አብርሃም አስታውቀዋል።

ክፍያው ላልተሰሩ ስራዎች ብቻ ሳይሆን ገና ይሰራሉ ተብለው ለሚታሰቡት መፈጸሙን አረጋግጠዋል።

በሜቴክ የሚሰራው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራ ከ30 በመቶ በታች በመሆኑ ስራቸውን እንዳጓተተባቸው የሳሊኒ ኮርፖሬሽን አማካሪ ሚኒስትር ሮበርት ማሪጊኒ ይህ ደግሞ ለተጨማሪ ክፍያ ጥያቄ እንደገፋው ገልጸዋል።

ሳሊኒ የጠየቀው ተጨማሪ ክፍያ 3 ነጥብ 259 ቢሊየን ብርና 338 ሚሊየን ዩሮ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ አስታውቀዋል።

አለም አቀፍ ስምምነት በመሆኑም ክፍያው የግዴታ እንደሚፈጸም አክለው ገልጸዋል።

ማንም ከሕግ በላይ ስላልሆነ አጥፊዎችን ተጠያቂ እናደርጋለን ያሉት የሜቴክ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ ለዚህ ብክነት ሃገራዊ ሃላፊነት መውሰድ ግዴታ እንደሆነ አረጋግጠዋል።