የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ይከናወናል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 27/2011)የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዳይከናወን የሚያደርግ ስጋት የለም ሲል የማዕከላዊ ስታስቲክስ ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሳፊ ገመዴ ለኢሳት እንደገለጹት በሚቀጥሉት ሁለት ወራት የተፈናቀሉት በሙሉ ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ የሚደረግ በመሆኑ ቆጠራው ላይ የሚፈጠር ችግር አይኖርም።

ከ1ሚሊዮን በላይ ተፈናቃይ የሚገኝባት ኢትዮጵያ ቆጠራውን ለማካሄድ የሰላምና የደህንነት ሁኔታው አስተማማኝ አይደለም የሚል ስጋት ከተለያዩ ወገኖች በሚሰጥበት በዚህን ወቅት የማዕከላዊ ስታስቲክስ ባለስልጣን ዘንድሮን እንደማይሻገር አስታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የሰላም ሚኒስቴር 1ሚሊዮን የሚሆኑ ተፈናቃዮችን ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ማድረጉን ገልጿል።

ከሁለት ወር ያነሰ ጊዜ ነው የቀረው። አሁንም በሚሊዮን የሚቆጠር ዜጋ ከቀዬው መንደሩ ተፈናቅሎ በመጠለያ ጣቢያዎች ይገኛል።

እንደመሰንበቻው ባይሆንም በአንዳንድ አባባቢዎች የእርስ በእርስ ግጭቶች መፍትሄ ሳያገኙ ቀጥለዋል።

ለማዕከላዊ ስታስቲክስ ባለስልጣን የትኛውም ችግር የህዝብና ቤት ቆጠራውን የጊዜ ሰሌዳ የሚያስቀይር አልሆነም።

ለኢሳት ቃለመጠይቅ የሰጡት የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሳፊ ገመዴ እንደሚሉት ስጋቶች እየተቀረፉ መምጣታቸውና የተቀሩትንም በመጪዎቹ ጊዜያት እልባት በመስጠት ቆጠራውን በታሰበለት ቀን ለማካሄድ በመንግስት በኩል አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው።

የማዕከላዊ ስታስቲክስ ባለስልጣን ለመጋቢት 29 ቀጠሮ የያዘለትን 4ተኛውን የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ማድረግ የነበረበት ባለፈው ዓመት 2010 ላይ እንደነበረ ነው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው የሚገልጹት።

ይሁንና ባለፈው ዓመት የነበረው የጸጥታ ሁኔታ ቆጠራውን ለማከናወን የሰላምና መረጋጋት ሁኔታው አስተማማኝ ባለመሆኑ ለዚህኛው ዓመት ተሸጋግሯል ብለዋል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ግን ባለፉት 11ወራት በእርስ በእርስ ግጭት፣ በድርቅና በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር እያሻቀበ መቷል።

ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉም ሆነ ከኦሮሚያ ወደ ሶማሌ ክልል የሸሹ ዜጎች ወደቦታቸው አልተመለሱም።

የሰላም ሚኒስቴር ዛሬ ወደ አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው መልሼአለሁ የሚል ሪፖርት ለምክር ቤት ማቅረቡ ታውቋል።

ሆኖም ሁለት ወር በማይሞላ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠር ተፈናቃይ ዜጋን ወደ መኖሪያው መመለስ የማይቻል እንደሆነ ታዛቢዎች ይገልጻሉ።

መንግስት የቆጠራውን ቀን ላለመግፋት በሚወስደው የጥድፊያ ርምጃ የበለጠ ቀውስ እንዳይፈጠር የሚሰጉ ወገኖችም አሉ።

አቶ ሳፊ ገመዴ የማዕከላዊ ሳታስቲክስ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ በቀሪው ጊዜያት ቀሪዎቹን ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው በመመለስና መረጋጋት በማስፈን ቆጠራውን ለማካሄድ የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል ይላሉ።

ስጋቱ አሁንም አለ። ክልሎች በየአስተዳደር ወሰናቸው የሚደረገው ቆጠራ ላይ ሙሉ ስልጣን የተሰጣቸው መሆኑ፣ የብሔርተኝነት ስሜት እየከረረ መምጣቱና ግጭቶች እንደአዲስ የሚያገረሹበት ምልክቶች እየታዩ መሆናቸው ቆጠራውን ተአማኒነት እንዳይኖረውና እንዳያስተጓጉለው ስጋታቸውን የሚገልጹት ጥቂት አይደሉም።

መንግስት ግን አሁንም ከአቋሙ ወደ ኋላ አላለም። ለመጋቢት 29 ዝግጅቱን እያካሄደ መሆኑን ቀጥሎበታል።