የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ መቋጫ ሳያገኝ አንድ ሳምንት እንዳለፈው ተገለጸ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 30/2010)ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ /ሕወሃት ለአራት ቀናት ያቀደው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ መቋጫ ሳያገኝ አንድ ሳምንት እንዳለፈው ተገለጸ።

ሆኖም ሕወሃት ስብሰባው ተጠናቋል ሲል መግለጫ አውጥቷል።

የሕወሃት ምንጮች በአደባባይ እንደጻፉት የማዕከላዊ ኮሚቴው ለመወያየት ከያዛቸው የተለያዩ አጀንዳዎች ግማሹን ያህል እንኳን ሳይወያይ አንድ ሳምንት ተቆጥሯል።

በስብሰባው ቀደምት የህወሃት መሪዎች መገኘታቸው በመክፈቻው ላይ የታየ ቢሆንም በዝርዝር ውይይቱ ስለመሳተፋቸው ግን የተገለጸ ነገር የለም።

ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ሕወሃት ባለፈው ሳምንት ሰኞ ጀምሮ በአራት ቀናት ይጠናቀቃል የተባለው ስብሰባ አለመጠናቀቁን የቅርብ ምንጮች ገልጸዋል።

ፓርቲው ስብሰባው ተጠናቋል በማለት ሰኞ ዕለት መግለጫ አውጥቷል።

በዚህም ስብሰባው ከመስከረም 22 እስከ መስከረም 28 ለሰባት ቀናት መካሄዱን ዘርዝሯል።ማዕከላዊ ኮሚቴው በስብሰባው የድርጅትና የመንግስትን የስራ አፈጻጸም መገምገሙንም አስታውቋል።

ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ስብሰባው ተጠናቀቀ በማለት መግለጫ ቢያወጣም የሕወሃት ምንጮችን ጠቅሰው ይፋ የሆኑ ሪፖርቶች እንዳመለከቱት የሕወሃት ስብሰባ አሁንም ቀጥሏል።

የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ሊወያይባቸው ከያዛቸው 6 ያህል አጀንዳዎች አንድ ሳምንት ያህል ባደረገው ስብሰባ ከሁለተኛው አልፎ ወደ ሶስተኛው መግባት አልቻለም።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ስብሰባው ተጨማሪ ቀናትን ሊወስድ እንደሚችል የሕወሃት ምንጮች እየገለጹ ይገኛሉ።

ፓርላማው ስራውን ሲጀምር አዲስ የካቢኔ ሹም ሽርን ጨምሮ አንዳንድ የስልጣን ብወዛዎች እንደሚኖሩ አስቀድሞ የተገለጸ ቢሆንም የሕወሃት ስብሰባ አለመጠናቀቁ ሂደቱን እንደገታው ተመልክቷል።

የአቶ አባዱላ ገመዳን የስራ መልቀቂያ ጥያቄን ጨምሮ በቀጣይ የሚወሰዱ ሀገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ እየተጠበቀ ሲሆን የሕወሃት ውሳኔ ለኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ከቀረበ በኋላ ስራ ላይ እንደሚውልም የፓርቲውን አሰራር የሚያውቁ ወገኖች ይገልጻሉ።