የህወሃት የግንባታ ኩባንያዎች የሚሰሩዋቸው ግንባታዎች በጥራት ችግርና በሙስና እየተወነጀሉ ነው

ሰኔ ፯ (ሰባት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የህወሃት የግንባታ ድርጅቶች በአማራ ክልል የሚሰሩዋቸው የግንባታ ስራዎች የጥራት ችግር ያለባቸው እንዲሁም ከተያዘላቸው የማጠናቀቂያ ጊዜ በላይ በማዘግየት በህብረተሰቡ ላይ ችግር እየፈጠሩ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
በክልሉ የህንጻ ግንባታና መንገድ ስራዎችን በስፋት የተቆጣጠሩት የህወሃት ድርጅቶች ስራቸውን ለምን እንዳላጠናቀቁ በአካባቢው ነዋሪዎችና አመራሮች ሲጠየቁ፣ በማዕከላዊ ደረጃ የሚገኙ የህውሃት አመራሮችን እንደመከታ በመጥራት በቂ መልስ እንደማይሰጡ ከክልሉ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በክልሉ በርካታ የህንጻና መንገድ ግንባታዎችን በመያዝና በማጓተት የሚታወቀው የህወሃቱ ሳት ኮን ድርጅት፣ በባህርዳር ከተማ ከሚሰራቸው ግንባታዎች መካከል አንዱ የሆነው የባህርዳር ዩኒቨርስቲ የዘንዘልማ ካምፓስ ህንጻ ከአመታት በፊት ስራው ይጠናቀቃል ቢባልም፣ እስካሁንም አልተጠናቀቀም። እርምጃ የሚወስድ አካል በመጥፋቱም ድርጅቱ በስራው ቀጥሎአል።
ሳት ኮን በዚሁ ስራ ላይ ተቀጥረው የሚሰሩትን ሰራተኞቸ ደሞዝ እስከ ሶስት ወር በማዘግየት እያጉላላ ይገኛል::የኪራይ መኪኖችንም ለስድስት ወራት ያህል ያለምንም ክፍያ በማሰራት ገንዘብ በመከልከል በተደጋጋሚ ክስ ቢከሰስም፣ ምንም ዓይነት ርምጃ ሳይወሰድበት በድርጊቱ መቀጠሉን ታዘቢዎች ይናገራሉ፡፡
ሳት ኮን ድርጅት ከአምስት ዓመታት በፊት ከደጀን መገንጠያ እስከ ፈለገ ብርሃን የጀመረው የመንገድ ስራ ከተገቢው ጊዜ በላይ መዘግየቱን የሚናገሩት የብቸና ከተማ ነዋሪዎች መንገዱ ተሰርቶ ሳይጠናቀቅ በመፈራረስ ላይ መሆኑንም ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡
የመንገድ ስራው በህዝቡ ግፊትና ተደጋጋሚ አቤቱታ በከፊል ተጠናቆ አገልግሎት ቢጀምርም፣ አንዳንድ የመንገድ አካባቢዎች አንድ ዓመት ሳያገለግሉ መበላሸታቸውን በመንገዱ የሚጠቀሙ አሽከርካሪዎች ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ በብቸና ከተማ የገነባው የውሃ ፍሳሽ ማስወገጃ ጥራት የሌለው በመሆኑ በመፈራረስ ላይ እንደሆነ የሚናገሩት የከተማዋ ከፍተኛ አመራር፣ ድርጅቱ ስራውን በማናለብኝነት በተያዘለት የማጠናቀቂያ ጊዜ ባለማጠናቀቁ ትራንስፖርት ፍሰቱን ማስተጓጎሉን ተናግረዋል፡፡
የሳትኮን መንገድ ስራ ድርጅት የ76 ኪሎ ሜትሩን ስራ ከየካቲት 2004 ዓም.ጀምሮ በሁለት ዓመት ለማጠናቀቅ በ528 ሚሊዮን ብር ውል ቢገባም፣ከ5 ዓመት በኋለም ስራውን አለማጠናቀቁን መረጃወች ያሳያሉ፡፡
በህወሃት ባለስልጣናት ይደገፋል በሚባለው ተክለብርሃን አምባየ የግንባታ ድርጅት የተሰራው የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ህንጻ በጥራት ጉድለት የተነሳ እስካሁን ድረስ ርክክብ አልተፈጸመለትም፡፡
በህንጻው ላይ የተገጠመው የፍሳሽ ስርዓት በጠቅላላ የተበላሸ መሆኑን ተከትሎ የፍሳሽ ማጠራቀሚያ ታንከሮች በየሳምንቱ እየሞሉ በማስቸገራቸው ሁሉም መጸዳጃ ቤቶች ያለ ውሃ እንዲሰሩ መደረጉ፣ የኤሌትሪክዕቃዎችና የቧንቧ ዕቃዎች የጥራት ችግር ያለባቸው መሆኑን በተቆጣጣሪ ድርጀቱ ባለሙያዎች በመረጋገጡ እና በሌሎችም በርካታ ችግሮች ሳቢያ ርክከቡን ደፍሮ ለመፈጸም የሞከረ ስራአስኪያጅ ባለመገኘቱ ርክክቡ ከአምስት አመት በላይ አለመፈጸሙን የውስጥ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡