የህክምና ባለሙያዎች የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 9/2011)በተለያዩ ከተሞች በህክምና ባለሙያዎች የተቃውሞ ሰልፎች ተደረጉ።

መንግስት ጥያቄችንን ለመፍታት ዝግጁ አይደለም በሚል በአዲስ አበባ፣ በደብረማርቆስ፣ በአክሱምና በሌሎች ከተሞች ተቃውሞ ሰልፎች መካሄዳቸውን የደረሰን መረጃ ያመልክታል።

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አንዳንድ የድህረ ምረቃ ተማሪዎች የተካሄደው አድማ ለሶስተኛ ቀን ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ህክምና ባለሙያዎች ማህበር አድማው ተገቢ አይደለም ሲል መግለጫ ሰጥቷል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን መመለስ የምንችለውን እየመለስን ነው፣ ከጥቅማጥቅሞች ጋር የተነሱትን ጥያቄዎች ደግሞ እንደመንግስት አቅም ወደፊት የሚታዩ ይሆናል ሲሉ ለኢሳት በሰጡት ቃለመጥይቅ ገልጸዋል።

የህክምና ባለሙያዎች በመንግስት የጤና ፖሊሲና በጥቅማጥቅም አንጻር ያነሷቸው ጥያቄዎች አሁንም ምላሽ ይሻሉ በሚል እያሰሙ ያሉትን ተቃውሞ ዛሬ ቀጥለው ሰላማዊ ሰልፎችን አድርገዋል።

በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሚገኙ አንዳንድ ተለማማጅ ሃኪሞችና የድህረምረቃ ተማሪዎች በስራ ማቆም አድማ ሶስተኛ ቀናቸውን በያዙበት በዛሬው ዕለት ባህርዳርና አክሱም የሚገኙ ባለሙያዎች በተቃውሞ ሰልፎች ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

የባህርዳር ፈለገ ሕይወት ሪፈራል ሆስፒታል ሀኪሞች፣ የጤና ባለሙያዎችና የዩኒቨርስቲው ተለማማጅ ሐኪሞች ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ የአስተዳደራዊ፣ ደመወዝና ጥቅማጥቅም ጥያቄዎችን በማንሳት አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

በአዲስ አበባ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሚሰሩ ሀኪሞችም ዛሬ ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ በሽተኞች እየተጎዱ ያሉት በሃኪሞች አድማ ምክንያት ሳይሆን በመንግስት የተበላሸ የጤና ፖሊሲ አማካኝነት ነው ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

በአክሱም፣ በደብረታቦር፣ በመቀሌና በደብረማርቆስም ተመሳሳይ የህክምና ባለሙያዎች የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገዋል።

መብታችንን መጠየቃችን ለጤናው ዘርፍ የተሳካ እንዲሆንና የታካሚዎችን ደህንነት ከመጠበቅ አንጻር ነው ብለዋል ሰልፈኞቹ።

ሃገር አቀፉ የህክምና ባለሙያዎች ማህበር መብታችንን ሊያስከብርልን አልቻለም በሚል ከማህበሩ እውቅና ውጪ ተቃውሞና የስራ አድማ የሚያደርጉት አንዳንድ የህክምና ባለሙያዎችና ተለማማጅ ሃኪሞች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለጥያቄዎቻቸው የሰጡት ምላሽ ክብራችንን የነካ፣መፍትሄ ለመስጠት በመንግስት በኩል ፍቃደኝነት እንደሌለ የሚያመለክት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህክምና ባለሙያዎች ማህበር ጉዳዩን በተመለከተ በአዲስ አበባ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የተነሱትን ጥያቄዎች እንደግፋለን፣ አድማውን አናበረታታም ብለዋል የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ገመቺስ ማሞ።

በህክምና ባለሙያዎች የተነሱትን የመብትና የጥቅማጥቅም ጥያቄዎች በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን መንግስት ምላሽ እየሰጠ ባለበት በዚህን ወቅት አድማና ተቃውሞ ማድረግ ተገቢ አይደለም ብለዋል።

መንግስት የአቅሙን መልስ እየሰጠ እንደሆነም ገልጸዋል።