የህንድ የጨርቃጨርቅና የልብስ አምራች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ነጻ መሬት ተሰጥቷቸው በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ የማግባባት ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ኢሳት (የካቲት 9: 2009)

በህንድ ጉብኝትን እያደረጉ ያሉ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የሃገሪቱ የጨርቃጨርቅና የልብስ አምራች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ነጻ መሬት ተሰጥቷቸው በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ማግባባት እያደረጉ መሆኑን የሃገሪቱ መገኛኛ ብዙሃን ዘገቡ።

በህንድ በኮንጉ-ናዱ ግዛት ስር በምትገኘው የትሪፑር ከተማ ጉብኝትን እያደረጉ ያሉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታደሰ ሃይሌ ህንዳዊያን ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መግባት ቢፈልጉም ነጻ መሬት እንደሚቀርብላቸው ቃል መግባታቸውን ዎርልድ ኦፍ ጋርመንት መጽሄት አስነብቧል።

የህንድ የጨርቃጨርቅ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ስራ ላይ ቢሰማሩ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ያለቀረጥ በሚቀርቡ የገበያ ፍላጎቶች ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ባለሃብቶች ገልጸዋል።

ህንዳዊያን የጨርቃጨርቅ ባለሃብቶች በሃገራቸው ያመረቱት ምርት ወደ አውሮፓ ከመላክ ይልቅ በኢትዮጵያ አምርተው ቢያቀርቡ የተሻለ ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሚኒስትሩ አቶ ታደሰ ሃይሌ ህንዳዊያን ባለሃብቶቹን ለማሳመን ሞክረዋል።

በኢትዮጵያ አሜሪካ የተለያዩ ምርቶችን ወደ ሃገሪቱ ያለቀረጥ እንዲያስገቡ የተለየ ዕድል ከሰጠባቸው የአለም ሃገራት ተርታ ብትሆንም በጨርቃጨርቅ ንግድ የተጠበቀውን ያህል ተጠቃሚ እንዳልሆነች ይነገራል።

ይሁንና አዲሱ የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ወደ አሜሪካ በሚገቡ የንግድ ሸቀጣሸቀጦች ላይ አዲስ ፖሊሲ ለመከተል መወሰናቸው በኢትዮጵያ ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ተብሎ ተሰግቷል።

ባለፈው አመት የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ አሜሪካ ለ40 ሃገራት የሰጠችው የንግድ ዕድል ለቀጣዩ 10 አመታት ቀጣይ እንዲሆን ቢወስኑም መመሪያው በፕሬዚደንት ትራምፕ ሊቀለበስ እንደሚችል የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።

በዚሁ ሁኔታ ስጋት ያደረባቸው የኢትዮጵያ ባለስልጣናት አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ቀጣይ የሆነውን የንግድ ዕድል ተጠቃሚነት ቀጣይ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን ለመረዳት ተችሏል።

በቅርቡ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ የትራምፕ አስተዳደር የአጎአ (AGOA) የንግድ ስምምነትን ቀጣይ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ይህንኑ ዕድል ለመጠቀም በርካታ የቱርክ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎችን ቢያቋቁሙም፣ ሃገሪቱ የታቀደውን ያህል ተጠቃሚ እንዳልሆነች የንግድ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

በቅርቡም ሁለት የቱርክ ባለሃብቶች ከመንግስት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ወስደው ያቋቋሙትን ፋብሪካ ጥለው ከሃገር መውጣታቸውን መዘገቡ ይታወሳል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ከመንግስት ጋር በሽርክና ሲሰራ የነበረው ሳይጊን-ዲማ የተሰኘ ፋብሪካ ውጤታማ ባለመሆኑ በቅርቡ ለጨረታ መቅረቡም አይዘነጋም።

ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል ተብሎ የነበረው ይኸው ፋብሪካ ከአንድ አመት በፊት 105ሺ ዶላር ብቻ ማስገኘቱን የንግድ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።