የሃዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ስጋት ላይ መውደቃቸውን ገለጹ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 5/2011) በሀዋሳና አካባቢዋ ኤጄቶ በሚል የሚጠራው ቡድን ከጠራው አድማ ጋር ተያይዞ በከተማዋ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ባለመኖሩ የከተማዋ ነዋሪው ስጋት ላይ መውደቁን ነዋሪዎች ገለጹ።

የሚያቀርቡት ጥያቄ ትክክል ቢሆንም እየሄዱበት ያለው አካሄድ ግን ትክክለኛ ያልሆነና የሌላውን መብት የሚገፍ ነው ብለዋል።

የሲዳማ አርነት ንቅናቄ በበኩሉ ኤጄቶ የጠራው አድማ ተጠንቶና ታስቦበት የተደረገ ነው፣እኛም ይህን አድማ እንደግፈዋለን ብሏል።

ይሄ እንዲሆን ያደረጉት ደግሞ የሲዳማ ህዝብ ያቀረበውን የክልል እንሁን ጥያቄ ምላሽ መስጠት ያልቻሉ አካላት ናቸው ብለዋል።

በሃዋሳ ከተማ ውጥረት የነበረው ከባለፈው አርብ ጀምሮ ነው ይላሉ የከተማዋ ነዋሪዎች።

በከተማዋ ከምሽት በኋላ ብዙም እንቅስቃሴ አይታይም ነበር ሲሉ ያክላሉ።አሁን ደግሞ በሃዋሳና በሲዳማ ዞን ኤጄቶ የሚባለው ቡድን በጠራው አድማ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፡ትምህርት ቤቶች፡የንግድ ሱቆችና ተመሳሳይ ተቋማት ተዘግተዋል።

ከዚህ ጋ ተያይዞ የከተማዋ ህዝብ በጭንቀት ከተማዋ ደግሞ ጭር ብላለች ይላሉ።

አገልግሎት ይሰጥ የነበረው የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክም በተከፈተበት የማህበራዊ ድረገጽ ዘመቻ እንዲዘጋ ተደርጓል።

የደቡብ መገናኛ ብዙሃን እንዲዘጋ የተከፈተው ዘመቻ ግን ሳይሳካ መቅረቱንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል

በከተማዋ ከተፈጠረው ውጥረት ጋር ተያይዞ የከተማዋ ነዋሪ በጭንቀት ውስጥ መሆኑንም ይናገራሉ።

ክልሉን እያስተዳደሩ ያሉ አካላት ከእነዚህ ቡድኖች የሚተላለፈውን መልዕክት በተመለከተም ከህዝብ ወገን ወግነው የሚያደርጉት አንዳችም ነገር የለም ይላሉ።

ስለዚህ መንግስት እንደመንግስት ህዝቡን የሚወክሉ አካላት እንዲያስተዳድሩ በማድረግ የህዝቡን ሰላም መስጠት አለበት ሲሉም አስተያየታቸውን ሰተዋል።

በግላቸው መመሪያ እያስተላለፉና የሰውን ሰላም አደጋ ውስጥ እየከተቱ ያሉ አካላትንም መንግስት አንድ ሊላቸው ይገባል ብለዋል።

የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ከፍተኛ አመራር ዱካእሌ ላሚሶ በበኩላቸው ኤጄቶ በመባል የሚጠራው ቡድን ያስተላለፈው የስራ ማቆም አድማ ትክክል   ነው ብለዋል።–ለዚህ ተጠያቂ የሚሆነው ላቀረብንው ጥያቄ ምላሽ ያልሰጠን አካል ነው በማለት።

የሲዳማ ሕዝብን ለዘመናት ይሄን ጥያቄ ሲያቀርባ ሲታገል ቆይቷል፣አሁን ደግሞ ጥያቄውን በህገመንግስቱ መሰረት አቅርቦ ምላሽ ቢጠብቅም ከሚመለከተው አካል ግን ምላሽ ማግኘት አልቻለም ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህም የተነሳ ተቋማት እንዲዘጉ በማድረግ ተቃውሞውን ማሰማት መርጧል ይላሉ።

የሲዳማ ህዝብ የክልል እንሁን ጥያቄን የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የሲዳማ ህዝብ የሚቀበለው ሃሳብ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የሲዳማ ህዝብ ይህን ጥያቄውን ሲያቀርብ ግን የሌሎችን መብት በመጋፋት አይደለም ሲሉም ተናግረዋል።