የሀዋሳ መምህራን የስራ ማቆም አድማ መቱ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 15/2010)የሀዋሳ ታቦር ሁለተኛ ደረጃ መምህራን ለአንድ ቀን የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸው ተገለጸ።

መምህራንን የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ለማድረግ በደቡብ ክልል መንግስት የወጣው መመሪያ ተፈጻሚ ሳይሆን ቤት እንዳገኘን ተደርጎ ሪፖርት መቅረቡና በመገናኛ ብዙሃን መነገሩ አስቆጥቶናል ያሉት መምህራን የአንድ ቀን ስራ በማቆም ወደክልሉ መስተዳድር በመሄድ ቅሬታቸውን ማቅረባቸው ተገልጿል።

በከተማዋ የሚገኙ ሌሎች ትምህርት ቤት መምህራንም እንዲቀላለቀሉ ተጠይቋል።

በሌላ በኩልም በዙር ሀዋሳ ለደረሰው የአባይ ዋንጫ መዋጮ መምህራን ገንዘብ አንሰጥም ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን በግዴታ ከደመውዛቸው ለመቁረጥ መታቀዱንም ለማወቅ ተችሏል።

ከአንድ ዓመት በፊት የደቡብ ክልል መንግስት አንድ አዋጅ ያወጣል። አዋጁ መምህራንን የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ተብሎ የተቀረጸ ነበር።

በአዋጁም መምህራን ሶስት አማራጮች ተሰጥቷቸው የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ ተባለ።

ይሁንና አዋጁ ከወረቀት አልፎ መሬት ላይ መውረድ ሳይችል ከቆየ በኋላ የመንግስት ባለስልጣናት መምህራን የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ሆነዋል የሚል ሪፖርት ማቅረባቸውንና ይህንንም የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ማሰራጨታቸው በመምህራኑ ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል።

በተለይ የሀዋሳ ታቦር ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን ቤት እንዳገኙ ተደርጎ ሪፖርት መቅረቡን ተከትሎ ተቃውሞ አሰምተዋል።

ቅሬታቸውን ይዘው እስከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ድረስ እንዳመሩ ያነጋገርናቸው አንድ መምህር ገልጸዋል።

ትላንት ሀሙስ የሀዋሳ ታቦር ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ መምህራን ስራ በማቆም ወደ ደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ማምራታቸውን የጠቀሱት መምህሩ ለጊዜው ርዕሰ መስተዳደሩን እንዳላገኙና እስከማክሰኞ ምላሽ እንደሚሰጣቸው ተነግሯቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል።

ማክሰኞ ምላሽ የማያገኙ ከሆነ የስራ ማቆም አድማ በድጋሚ ሊመቱ እንደሚችሉ ኢሳት ያነጋገራቸው ሌሎች መምህራንም ገልጸዋል።

ከታቦር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን በተጨማሪ በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ መምህራንም ተመሳሳይ አቋም ለመውሰድ በመምከር ላይ ናቸው ተብሏል።

በሌላ በኩል የሀዋሳ መምህራን ለአባይ ግድብ ገንዘብ በአስገዳጅነት እንዲሰጡ ሊደረግ መሆኑ ተቃውሞ አስነስቷል።

በዙር ሀዋሳ የደረሰው የአባይ ዋንጫ ከፍተኛ ገንዘብ ከህዝብ እንዲሰበሰብ በመታቀዱ በየቦታው የገንዘብ መዋጮ በስገዳጅነት እየተከናወነ ሲሆን በቅርቡ የሀዋሳ ነጋዴዎች ቅሬታ ማቅረባቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

መምህራንም ተመሳሳይ መዋጮ የተጠየቁ ሲሆን አንከፍልም በማለታቸው ከመንግስት ጋር ፍጥጫ ውስጥ መግባታቸው ታውቋል።

የአንድ ወር ደመወዝ ከመምህራን ላይ በአስገዳጅነት ለመውሰድ መታቀዱንም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከዚህ ቀደም በሲዳማ ዞን የጭኮ መምህራንም ለአባይ ግድብ መዋጮ አንሰጥም በማለት የስራ ማቆም አድማ እስከማድረግ መደረሳቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው።