ወደ ኬንያ የገቡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር 50 ሺህ ደረሰ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 3/2010) በሞያሌ እየተፈጸመ ያለውን ጭፍጨፋ በመሸሽ ኬኒያ የገቡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር 50 ሺህ መድረሱ ተገለጸ።

የአጋዚ ወታደሮች የሚፈጽሙት ግድያም ቀጥሏል።

ወደ ኬኒያ በሽሽት ላይ በነበሩ የሞያሌ ከተማ ነዋሪዎች ላይ ትላንት ተኩስ የከፈተው የአጋዚ ሃይል 2 ሰዎች መግደሉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በሌላ በኩል የሞያሌው ጭፍጨፋ በስህተት የተፈጸመ ነው የሚለው የአገዛዙ መግለጫ ቁጣን ቀስቅሷል።

ቅዳሜ  ለሞያሌ ነዋሪዎች ጥሩ ቀን አልነበረም።

በጠዋት በወትሮው እንቅስቃሴዋ ላይ ተጠምዳ የነበረችው ሞያሌ ድንገት የታጠቀ ሰራዊት ዘመተባት።

የአጋዚ ሰራዊት በጠራራ ጸሀይ ነዋሪውን እያሳደደ፣ ሱቅና መደብሮችን እያከፈተ በጥይት መደብደብ ጀመረ።

በትንሹ 10 ነዋሪዎች ወዲያውኑ ወደቁ። በአንዳንዶች መረጃ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 17 እንደሆነ ይገለጻል።

ሞያሌ ሳይታሰብ ድንገት በዘመተባት የአጋዚ ሰራዊት ዕልቂት ተፈጸመባት።

ከ30 በላይ ሰዎች ቆስለው ወደ ህክምና ማዕከላት ተወስደዋል። ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው እንዳሉ የጠቀሱት የኢሳት ምንጮች ምናልባትም የሟቾቹ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።

ከተገደሉት መሀል በአርዓያነታቸው በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ተሸላሚ የሆኑ የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር እንደሚገኙበትም ተገልጿል። ሁኔታው በመላው ዓለም ኢትዮጵያውያንን ያስደነገጠና ያሳዘነ ሆኗል።

ጭፍጨፋው በተፈጸመ ዕለት መግለጫ የሰጠው ኮማንድ ፖስት ግድያው የተፈጸመው በስህተት ነው ብሏል።

የኦነግ ታጣቂዎችን ለመምታት የተሰማራው ሃይል በስህተት ሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያ ፈጽሟል የሚል መግለጫ የሰጠው ኮማንድ ፖስቱ 5 ወታደሮችና አዛዣቸው በምርመራ ላይ ናቸው ብሏል።

ይህ የአገዛዙ መግለጫ ከጭፍጨፋው ድርጊት በላይ ብዙዎችን አሳዝኗል።

ሱቅ እያስከፈቱ ግድያ መፈጸማቸውን እየታወቀ በስህተት ነው የሚለው መግለጫ የአገዛዙን የጭካኔ መጠን የሚያሳይ ነው ሲሉም መግለጫውን በማውገዝ አስተያየት የሰጡ በርካታ ናቸው።

ለኢሳት በደረሰው መረጃም ትላንት ሶስት ተጨማሪ ሰዎች ተገድለውዋል።

የአጋዚን ጥቃት በመሸሽ ወደኬኒያ እየተሰደዱ በነበሩ የሞያሌ ከተማ ነዋሪዎች ላይ ተኩስ ተከፍቶ ሁለት ሰዎች መገደላቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ሽሽት ላይ ያሉትን ነዋሪዎች በሄሊኮፕተር ጭምር በታገዘ ዘመቻ ለማስፈራራት የተሞከረ ቢሆንም ህዝቡ ወደኋላ ሳይመለስ ኬኒያ ድንበር ዘልቆ ጋምቡ በሚባል አካባቢ መስፈሩንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በስህተት ነው የሚል መግለጫ ከተሰጠም በኋላ ግድያው መቀጠሉን የሚገልጹት የኢሳት ምንጮች ትላንት ምሽትም አንድ የሞያሌ ከተማ ነዋሪ በአጋዚ ወታደሮች መገደሉን ጠቅሰዋል።

ወንድማገኝ አዱኛ የተባሉ ነዋሪ በ10ጥይቶች ተደብድበው የተገደሉ ሲሆን አስክሬናቸው ከወንዝ ተጥሎ መገኘቱን ለማወቅ ተችሏል።

ሌላ ወጣትም በሁለት ጥይት ተመቶ መቁሰሉንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

የአጋዚን ጭፍጨፋ በመሸሽ ወደ ኬኒያ የገቡ ዜጎች ቁጥር 50 መድረሱን የጀርመን ድምጽ ሬዲዮ በዘገባው አስፍሯል።

የሞያሌ ከተማ ነዋሪዎች በአገዛዙ የደህንነት ሰዎች ወከባ እየደረሰብን ነው ሲሉ ስጋታቸውን መግለጻቸው እየተነገረ ነው።

የኬኒያ መንግስት ጥበቃ እንዲያደርግላቸውም ጠይቀዋል። ኬኒያ ሸሽተው ለተጠጓት ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እያደረገች መሆኑ ታውቋል።

የኬኒያ ቀይመስቀል መሰረታዊ የምግብና መጠለያ አቅርቦቶችን በመስጠት ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ሌላው ተጨማሪ የአጋዚ ጦር የተዘጋውን መንገድ እየከፈተ ዛሬ ገብቷል።

ባለፈው ወታደሮች ከተሰወሩ በኋላ ለተከታታይ ቀናት የወታደር ፕወዛ የተደረገ ሲሆን በቅርቡም ከተለያዩ ስፍራዎች አዳዲስ ወታደሮች ተቀይረው ገብተዋል።

ከዛው የቆዩትም በተለያዩ ስፍራዎች እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።