ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡና ከሃገር እንዳይወጡ እገዳ የተጣለባቸው ዜጎች ቁጥር 7 ሺ ያህል ነው ተባለ

          (ኢሳት ዲሲ–ጥር 9/2011) በቀደሞው የደህንነት ሃላፊ በአቶ ጌታቸው አሰፋ የስልጣን ዘመን ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡና ከሃገር እንዳይወጡ እገዳ የተጣለባቸው ዜጎች ቁጥር 7 ሺ ያህል እንደነበር ተገለጸ።

          የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እንደገለጹት እገዳ የተጣለባቸው ዜጎች ላይ ማጣራት እየተካሄደና ርምጃም እየተወሰደ መሆኑም ታውቋል።

          በዚህም በሶስት ሺ ዜጎች ላይ የተጣለው እገዳ መነሳቱ ተመልክቷል።

          ከሀገር መውጣትና ወደ ሀገር መግባት እንዳይችሉ እገዳ የተጣለባቸው ዜጎች ቁጥር ሰባት ሺ እንደነበር ታውቋል።

ከነዚህ ውስጥ ደግሞ ከ3ሺህ በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያይውያን ላይ የተጣለው እገዳ ተጣርቶ እንዲነሳ መደረጉን ነው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ይፋ ያደረገው።

እገዳው ተጥሎ የነበረው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደነበርም ተገልጿል።

ዛሬ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮችና የሰላም ቋሚ ኮሚቴ አባላት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትን በጎበኙበት ወቅት በተደረገው ገለጻ ላይ እንደተመለከተው ተቋሙ በፖለቲካ ወገንተኝነት ከህግ ውጭ ዜጎች ወደሀገር ቤት እንዳይገቡና ከሀገርም እንዳይወጡ እገዳ ሲጥል ቆይቷል።

በዚህም 7ሺህ ዜጎች የእገዳው ተጎጂ እንደሆኑ ተገልጿል። ተቋሙ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ድብቅ ሆኖ መቆየቱም ነው የተመለከተው።

           የፓርላማ አባላቱ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤትን በጎበኙበት ወቅት ዋና ሃላፊው ጄኔራል አደም መሃመድ እንደገለጹት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት የሚስጥር መስሪያ ቤትነቱ የሐገር እንጂ የፓርቲ ወይንም የሆነ ቡድን አይደለም።

          በሌላ በኩልም መንግስታዊዎቹ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመግታት ባደረገው እንቅስቃሴ 2 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላርን ጨምሮ የተለያዩ ሐገራት ገንዘቦችንም በቁጥጥር ስር አውሏል።

          ከ32ሺ በላይ የጦር መሳሪያዎች መያዛቸውንም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ሃላፊዎች ገልጸዋል።

          ይህ በእንዲህ እንዳለም የአዲስ አበባ ፖሊስ በሰጠው መግለጫ 88ሺ የአሜሪካን ዶላርን ጨምሮ የተለያዩ የውጭ ሃገራት ገንዘቦችን በ6 ወራት ውስጥ መያዙን ትላንት ገልጿል።

          2ሺ ያህል ሕገወጥ የጦር መሳሪያ መያዙንም ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።