ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 29/2011) ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ከሰባት ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ።

ወይዘሪት ብርቱካን አዲስ አበባ ሲደርሱም ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም ደማቅ አቀባበል እንዳደረጉላቸው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ወይዘሪት ብርቱካን በመንግስት ጥሪ ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ሲሆን በከፍተኛ የሃላፊነት ቦታ እንደሚመደቡም ለማወቅ ተችሏል።

ዳኛ ናቸው። ፖለቲከኛም እንዲሁ። በሁለቱም መስኮች የገዘፈ ስም የያዙ፣ ዋጋም የከፈሉባቸው፣በብዙዎች ዘንድ ጥንካሬአቸውና መስዋዕትነታቸው በአርያነት የሚነሳላቸው ናቸው።

የተወለዱት በአዲስ አበባ ነው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በህግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል።

ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ በሕዝብ አስተዳደር ወስደዋል። –ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ።

ፖለቲካውን ከመቀላቀላቸው በፊት በአዲስ አበባ ፌደራል ፍርድ ቤት ሶስተኛ ወንጀል ችሎት ዳኛ ሆነው አገልግለዋል።

በወቅቱ በሙስና ወንጀል እስር ቤት የሚገኙትን የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ስዬ አብረሃን ጉዳይ እንዲመለከቱ ጉዳዩ ቀርቦላቸው ነበር።

በብዙዎች ዘንድ የፖለቲካ እስር ተደርጎ የሚገለጸውና ከአቶ መለስ ዜናዊ በተፈጠረ ልዩነት ሙስና ሰበብ ተደርጎ እንደታሰሩ የሚነገርላቸውን የአቶ ስዬን ጉዳይ መመለከት ለዳኛ ብርቱካን የጥንካሬያቸው መለኪያ፣ ለሙያቸው ታማኝነትን የሚያሳዩበት አጋጣሚ የተፈጠረ ነበር።

ወይዘሪት ብርቱካን የአቶ ስዬን ጉዳይ እነመለስ ዜናዊ በፈለጉት መንገድ ሊመለከቱት አልቻሉም።

ለአቶ ስዬ የዋስትና መብት እንዲፈቀድላቸው ብይን ሰጡ። ይህ ውሳኔያቸው በአራት ኪሎ ቤተመንግስት ቁጣን ያስነሳ ሆነ።

አቶ መለስ የፍርድ ቤትን ውሳኔ በመተላለፍ አቶ ስዬ እግራቸው ከእስር ቤት ሳይወጣ በአንድ ሌሊት ህግ አርቀቀው እዚያው እስር ቤት እንዲሰነብቱ አደረጓቸው።

የወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ አቋም ለብዙዎች የጥንካሬና የታማኘት ተምሳሌት ሆኗል።

ወይዘሪት ብርቱካን ወደ ፖለቲካው የመጡት በ1997 ምርጫ ዋዜማ ላይ ነበር።

በቀስተደመና ፓርቲ በኋላም ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ውስጥ በመሳተፍ በወቅቱ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠቀሱ ፖለቲከኞች አንዷ ለመሆን ችለዋል።

የ1997 ምርጫ ቀውስን ተከትሎ በህወሃት አገዛዝ ሃገር መክዳት በሚል ወንጀል ተከሰው ለሁለት ዓመት በእስር የቆዩት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በአቶ መለስ ዜናዊ የተዘጋጀውን የይቅርታ ሰነድ አልፈርምም ብለው በአቋማቸው ከጸኑት መካከል የሚነሱ ናቸው።

ከእስር ከተለቀቁ በኋላ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን በመመስረትና በመምራት በፖአለቲካው ላይ ቆይተዋል።

ከእስር ቤት የወጡበትን ትክክለኛ ምክንያት ስውዲን ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በስብሰባ ላይ በመግለጻቸው በድጋሚ ለእስር ተዳርገዋል።

እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2002 በድጋሚ ከእስር ከወጡ በኋላ ወደ አሜሪካ በመምጣት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በመስራት ቆይተዋል።

ላለፉት ስድስት ዓመታት ከፖለቲካው ርቀው የቆዩት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ ወደ ሀገርቤት ገብተዋል።

ዛሬ አዲስ አበባ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን በትውልድ ሰፈራቸው አዲስ አበባ ፈረንሳይ ለጋሲዮን በልዩ ፕሮግራም የአቀባበል ስነስርዓት ተካሂዶላቸዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተገኙበት የጀግና አቀባበል የጠበቃቸው ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ህዝብ ለማገልገል የጀመሩትን ተግባር ለመቀጠል ወደ ሀገር ቤት እንደሚገቡ ተናግረዋል።

ሁኔታዎች በመለወጣቸው ወደ ሃገር መመለሳቸውን ገልጸዋል።

ወይዘሪት ብርቱካን በተቋማት ግንባታ ላይ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚችሉም አስታውቀዋል።

የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በዶክተር አብይ መንግስት ከፍተኛ የሃላፊነት ቦታ ይሰጣቸዋል።

ምናልባትም የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር ሊሆኑ እንደሚችሉ ምንጮች ካደረሱን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።