ካለፉት 6 ወራት ወዲህ በደሴ ከተማ የተከሰተው የውሃ እጥረት ተባብሷል

ሰኔ ፮ (ስድስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የደቡብ ወሎ ዞን ዋና ከተማ የሆነችው የደሴ ከተማ ካለፉት ስድስት ወራት ጀምሮ በከፍተኛ የመጠጥ ውሃ እጥረት መቸገሯን የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ። ለውሃ ስርጭቱ መቋረጥ የመብራት እጥረት መፈጠሩን መስተዳድሩ በምክንያትነት ይጠቅሳል። ነዋሪዎች አንድ ጀሪካን ውሃ እስከ አስር ብር ለመግዛት ተገደዋል። ለተጨማሪ ወጪዎች ከመዳረጋቸው በተጨማሪ የምንጭ ውሃ በአምራጭነት በመጠቀማቸው ለውሃ ወለድ በሽታዎች መጋለጣቸውን ነዋሪዎቹ በምሬት ይናገራሉ።
የከተማዋ መስተዳድር የነዋሪዎቹን ችግር ለመፍታት ከቃል የዘለለ የተግባር እንቅስቃሴ ሲደረገ አለመታየቱ ነዋሪዎቹን አሳዝኗል። የመስተዳድሩ አካላት አቅም አለመኖር፤ በቴክኒክ ሰዎች እና በፖለቲካ ሰዎች መሃከል፣ ልዩነቶች እየሰፉ መምጣታቸው ለችግሩ መባባስ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ምንጮቻችን ገልጸዋል። ”በውሃ ጥም ልናልቅ ነው መፍትሔ ስጡን” በማለት በኮሚቴ አማካኝነት ጥያቄዎቻቸውን ቢያቀርቡም የከተማው ከንቲባ የሕዝቡን ብሶት ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም።
በተጨማሪም በ2007 ዓ.ም የተጀመረውና አንድ ኪሎ ሜትር የማይሟላው የደሴ ከተማን መሃል ለመሃል የሚከፍለው ከዞኑ መስተዳድር እስከ ተቋም ድረስ የሚዘልቀው መንገድ እስካሁን ድረስ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ አልተጠናቀቀም። ማዘጋጃ ቤቱ በቂ ማሽነሪዎች እያሉት እንዴት ይህን ያህል ጊዜ ሊወስድበት እንደቻለ ምክንያቱን ማወቅ አልተቻለም። የመንገዱ ወቅቱን ጠብቆ አለመጠናቀቁ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እየፈጠረ መሆኑን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።