ከ120 በላይ አዳዲስ ዳኞች ተሾሙ

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 2/2010) የፍትህ ስርአቱን ለማሻሻል ያስችላሉ የተባሉ ከ120 በላይ አዳዲስ ዳኞች ተሾሙ።

የዳኞቹ ሹመት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ውድቀት ከደረሰባቸው ተቋማት አንዱ የሆነውንና የስርአቱ የፖለቲካ መሳሪያ ነው የሚባለውን የፍትህ ስርአት ለማሻሻል ነው ተብሏል።

በሳምንቱ መጨረሻ ቅዳሜ ፓርላማው ሹመታቸውን ካጸደቀላቸው ዳኞች ውስጥ ከ40 የሚበልጡት ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደሆነም ታውቋል።

ፓርላማው ለእረፍት ከመውጣቱ በፊት በሳምንቱ መጨረሻ ሹመታቸውን ያጸደቀላቸው 123 ዳኞች ናቸው።

ከነዚህ ውስጥ 74ቱ ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን 49 የሚሆኑት ደግሞ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት መሾማቸው ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ለሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ያቀረቡትን አዲስ እጩ ፓርላማው ማጽደቁ ታውቋል።

ዶክተር እንዳለ ሃይሌ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ዋና ሃላፊ ሆነው ሲሾሙ ወይዘሮ ፎዚያ አህመድ ደግሞ ከሃላፊነት ተነስተዋል።