ከፍተኛ የጦር አዛዦች ተሰናበቱ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 30/2011) በሰራዊቱ ውስጥ የተጀመረውን የለውጥ ርምጃ ለማጠናከር በርካታ ጄነራሎችን ጨምሮ ከ160 በላይ ከፍተኛ የጦር አዛዦች ከሰራዊቱ መሰናበታችውን የቅርብ ምንጮች ለኢሳት ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም ጎንደር ከተማ ላይ ትናንት በሰጡት መግለጫ ባለፉት 7 ወራት ከተሰሩ ስራዎች ትርጉም ያለውና መሰረት የረገጠ ስራ የተሰራው በሰራዊቱ ውስጥ እንደሆነ ገልጸዋል።

ፋይል

የሰራዊቱን አመራር ለማሰባጠር በተወሰደው ርምጃ የተነሱት ወታደራዊ ሃላፊዎች በፈቃደኝነት እንደለቀቁም ገልጸዋል።

ባለፉት 7 ወራት ትርጉም ያለው የማሻሻያ ርምጃ የተወሰደው በሃገር መከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገልጸዋል።

በተቋሙ ውስጥ የቀየርነው ሚኒስትሩን ብቻ ሳይሆን ተልዕኮውንም ጭምር ቀይረናል ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሌላው ስለቀበሌውና ስለመንደሩ ሲያላዝን ኢትዮጵያ ባለቤት ባጣችበት ወቅት ዕውነተኛው ኢትዮጵያዊነት የሚንጸባረቀው በሃገር መከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ ነው ብለዋል።

ዶክተር አብይ አህመድ በጎንደር ከተማ ከሕብረተሰቡ ከተውጣጡ ወገኖች ጋር ትናንት ባደረጉት ውይይት የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተውላቸውም ምላሽ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጡ ከመጣበት ካለፉት 7 ወራት ወዲህ ትርጉም ያለውና መሬት የረገጠ ስራ የተሰራው በሃገር መከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።

የሰራዊቱ አመራር ላይ የሚታየውን የብሄረሰብ አለመመጣጠን ለማስተካከል በቂ ስራ መሰራቱን ግልጽ አድርገዋል።

በዚህም የተነሳ ከክፍለጦር አዛዥነት እስከ እዝ ኣዛዥነት በአንድ ስፍራ ከአንድ በላይ የተመሳሳይ ብሔረሰብ ተወላጆች እንዳይኖሩ መደረጉን አብራርተዋል።

በርካታ የአንድ ብሔረሰብ ተወላጆች የሚበዙበትን ቦታ ለማስተካከል በተወሰደው ርምጃ ስልጣን የሚለቁትም ተባባሪ ሆነው መገኘታቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገልጸዋል።

በሃገር መከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ የተካሄደው ሪፎርም ውጤቱ በሂደት እንደሚታይም አስረድተዋል።

እውነተኛ ኢትዮጵያዊነት ያለው በመከላከያ ውስጥ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሌላው ስለመንደሩና ስለቀበሌው ሲያላዝን ኢትዮጵያዊነት እየተገለጸ ያለው በሃገር መከላከያ ሰራዊት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሁሉም ስለመንደሩ የሚጨነቅባት ባለቤት ያጣች አሳዛኝ ሃገር ሆናለች ሲሉም ቁጭታቸውን ገልጸዋል።

መከላከያ ውስጥ ግን ኢትዮጵያዊነት መኖሩን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከወሰን ጋር ተያይዞ ለተነሳባቸው ጥያቄም ባለሙያዎችና የሃገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የሚሳተፉበት ኮሚሽን ጥናት እንደሚያደርግበትም አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰራዊቱ ውስጥ በጀመሩት ሪፎርም በርካታ ጂኔራሎችና ከ160 በላይ የሚሆኑ የጦር መኮንኖች የተሰናበቱት በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ሲሆን ቀደም ሲልም ጠቅላይ ኢታማጆር ሹሙን ጄኔራል ሳሞራ የኑስን ጨምሮ ሌሎች መሰናበታቸው ይታወሳል።