ከኢትዮጵያ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ ተገለጸ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 12/2011) ከኢትዮጵያ ወደ ተለያዩ የውጭ ሃገራት፣ ከገጠር ወደ ከተማና ከክልል ወደ ክልል የሚሰደዱ ሰዎች ብዛት መጨመሩን እና  ከፍተኛ መሆኑ መረጋገጡን  በምሥራቅና በደቡብ አፍሪካ የማህበራዊ ሳይንስ ምርምር ተቋም አስታወቀ፡፡

ተቋሙ ላለፉት አምስት ዓመታት ባደረገው ምርምር ስደትን ሕግ በማውጣትና ድንበርን በመዝጋት ማስቆም እንደማይቻል አረጋግጭላሁ ብሏል።

ፋይል

‹‹በኢትዮጵያ ስደትን የሚያመቻቹ የተለያዩ አካላት›› በሚል ርዕሰ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የምርምሩ ባልደረባና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህር ዶክተር ፈቃዱ አዱኛ  ለሪፖርተር እንደገለጹት  ስደት የሚካሄደው በሕጋዊና  በሕገወጥ መንገድ ነው፡፡

እናም  ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቆም ሕግ አውጥቶ፣ ድንበር ዘግቶና ግብረ ኃይል በማቋቋም ለማስቆም ጥረት ቢደረግም፣ ሊያስቀረው እንዳልተቻለ በተደረገው ምርምር ተረጋግጧል ነው ያሉት፡፡

ሕገወጥ የሰዎች ስደት የሚፈጸመው በብዙ ተዋናዮች መሆኑንም ዶክተር ፈቃደ  ገልጸዋል።

በመተማና በሞያሌ ያሉት መሸጋገሪያ ድንበሮች መዝጋት ቢቻል በሌሎች በማይታወቁ መውጫ አቅጣጫዎች ስደቱ ተባብሶ እንደሚቀጥል፣ በተለይም ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በተደረገ ጥናት ሊታወቅ እንደቻለም ነው ያስታወቁት፡፡

የመውጫ ድንበሮች ሲዘጉም ሆነ ሲከፈቱ ወጪ እንዳላቸው፣ ነገር ግን ሲዘጋ ከሚመደበው በጀት ይልቅ ሲከፈት የሚመደበው እጅግ ያነሰ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

ሰው ድንበር ዘሎ ለመሄድ እስከተነሳ ድረስ መሸጋገሪያ ድንበሮችን ዘግቶ ማስቆም እንደማይቻል  ተመራማሪው አስታውቀዋል።

ስደትን ለማስቆም የተሻለ ሆኖ የተገኘው መጀመሪያ ስደት የሚበዛባቸውን አካባቢዎች መለየት ነውም ብለዋል።፡

ስደት የሚጀመረው ከቤተሰብ በሚደረግ ግፊት፣ በደላሎች፣ በኤጀንሲዎችና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ጭምርና እስከ ውጭ አገር ድረስ ባሉ የተለያዩ አካላት በመሆኑ መከላከል አስቸጋሪ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በምርምር ጥናቱ እንደተመለከተው መንግሥት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ዘመቻ ከፍቶ ለማስቆም እየሞከረ ነው።

በምርምር የተገኘው ውጤት በአገር ውስጥ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በማቋቋምና በመደገፍ፣ ወደ ውጭ አገራት የሚደረግን ስደት ማስቆም እንደሚቻል ያመለክታል።

በምሥራቅና በደቡብ አፍሪካ የማኅበራዊ ሳይንስ ምርምር ተቋም  ከገጠር ወደ ከተማና ከትንሽ ከተማ ወደ ትልቅ ከተማ፣ እንዲሁም ከክልል ወደ ክልል በሚደረገው ስደት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡