ከአቢሲኒያ ባንክ የተዘረፈው ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ተያዘ

(ኢሳት ዲሲ–ነሀሴ 6/2010) በአቢሲኒያ ባንክ ከ5ሚሊዮን ብር በላይ ተዘርፎ በኋላ ላይ መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

ቦሌ መድሃኒያለም ቤተክርስቲያን አካባቢ ከሚገኘው የአቢሲኒያ ባንክ ቴሌ መድሃኒያለም ቅርንጫፍ 5 ሚሊየን ስድስት መቶ ሺህ ብር ተዘርፎ በፖሊስ እና በአካባቢው ማህበረሰብ ትብብር ዘራፊዎቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አረጋግጧል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ እንደገለጹት ዘረፋው የተፈፀመው የድርጅቱ የጥበቃ ሰራተኛ ከነበሩት ግለሰብ ጋር ሌሎች ሁለት ግለሰቦች ተባብረው ነው።

በአሁኑ ጊዜ ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው አጠቃላይ የተወሰደው ገንዘብም ተመልሷል ብለዋል።

የአቢሲኒያ ባንክ የማርኬቲንግ፣ የኮሚኒኬሽንና ኦፕሬሽን ሥራ አስኪያጅ  አቶ አስቻለው ታምሩ በበኩላቸው የዘረፋ ሙከራው የተፈፀመው መኪና ይዘው በመደራጀት መሆኑን ገልጸዋል።

በወንጀሉ ላይ ተሳትፎ ነበራቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሌሎች ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ነው የተናገሩት።

ቢቢሲ የአማርኛው አገልግሎት ስለተጠርጣሪዎቹ እንደዘገበው አንድ ቪትዝ መኪና መጥታ ከሌላ መኪና ጋር በኃይል ከተላተመች በኋላ ግጭቱን ያደረሰው መኪና ለማምለጥ ሲሞክር በአቅራቢያው በነበሩ ሰዎች ሊያዝ ችሏል።

“መኪናዋ መሄድ ከነበረባት በተቃራኒው አቅጣጫ ነበር የመጣችው” የሚሉት የአይን ምስክሮቹ በግጭቱ ምክንያት  ከሃምሳ ሜትር በኋላ እንደቆመች ገልጸዋል።

ቀጥሎም ሾፌሩ በፍጥነት በመውረድ ወደፊት በመሮጡና ጋቢና የነበረው ሌላኛው ተሳፋሪም በተመሳሳይ አቅጣጫ በመሮጣቸው በአካባቢው የነበሩ ሰዎች በመጮሃቸው ተጠርጣሪዎቹ ሊያዙ ችለዋል።

ከመኪናዋ የኋላ በርም ጥቁር ሌዘር የለበሰ ሰው በእጁ ጩቤ ይዞ በመውጣት ሊያስፈራራ ቢሞክርም  ሳይሳካለት ቀርቶ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል።

ግጭቱን ያደረሰችው መኪና ውስጥም በማዳበሪያ የተዘረፈ ከ5 ሚሊየን ስድስት መቶ ሺህ ብር በላይ ሊገኝ ችሏል። REDAI