ከአማሮ ወረዳ የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ጉማይዴ ገቡ

ከአማሮ ወረዳ የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ጉማይዴ ገቡ
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 19 ቀን 2011 ዓ/ም ) ከአማሮ ወረዳ ቡኒቲ ቀበሌ የተፈናቀሉ በርካታ የአማራ ተወላጆች በሰገን ዞን ዋና ከተማ ጉማይዴ ላይ መስፈራቸውን ወኪላችን ገልጿል።
ነዋሪዎች እንደሚሉት በጉማይዴ ከተማ ጳጉሜ 2 ቀን 2010 ዓም በነበረው ሰልፍ ላይ የአማራ ተወላጆች ሰልፍ ሲወጡ የኮይሬ ተወላጆች ሰልፍ ባለመውጣታቸው የተጀመረው ጸብ፣ ጥቅምት 16 ቀን 2011 ዓም በ2 የአማራ ተወላጆች ላይ የተፈጸመው ድብደባ ተባብሶ በአማራ ተወላጆች ማሳ እና እንስሳት ላይ ጥቃቱ ሲጨምር፣ በርካታ ሴቶች፣ ህጻናትና አቅመ ደካሞች አካባቢውን ለቀው ወደ ጉማይዴ ተሰደዋል።
የጉማይዴ ከተማ ነዋሪዎች ለተፈናቃዮች ምግብ እያቀረቡላቸው ሲሆን፣ የመከላከያ ሰራዊት ገብቶ ግጭቱን በመቆጣጠሩ በሰዎች ህይወት ላይ ይደርስ የነበረውን አደጋ መቀነሱን ወኪላችን ገልጿል። ከሁለቱም ወገኖች የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች የማስታረቅ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ወከሎቻችን ያነጋገሯቸው ተፈናቃዮች ተናግረዋል።