ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ ተያዘ

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 14/2011)ቀጣዩን ሐገር አቀፍ ምርጫ በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ መያዛቸው ተገለጸ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ዛሬ ይፋ ባደረገው የጥሪ ደብዳቤ በቀጣዩ ማክሰኞ ህዳር 18/2011 በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በሚካሄደው የውይይት መድረክ የሁሉም የፖለቲካ አመራሮች ተጋብዘዋል።

“በሃገራችን ስለተጀመረው የዲሞክራታይዜሽን ጉዞና በሚቀጥለው አመት የሚደረገውን ሃገራዊ ምርጫን ነጻና ፍትሃዊ ለማድረግ ሊወሰዱ በሚገባቸው የሪፎርም ስራዎች ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ጋር ይወያያሉ”በማለት ጥሪ የሚያቀርበው ደብዳቤ መሳተፍ የሚፈልጉ ሁሉ አስቀድመው እንዲመዘገቡ ያሳስባል።

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ በተመረጡ ማግስት የቀረበው ጥሪ ሌሎች የምርጫ ቦርድ አባላትን በመምረጡ ሒደት ላይ ጭምር ለመወያየት ሳይሆን እንዳልቀረም ታምኖበታል።

ዶክተር አብይ አህመድ ትላንት በፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ ሌሎች የምርጫ ቦርድ አባላትን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በመወያየት እንደሚመርጡም መግለጻቸው ይታወሳል።

የምርጫ ቦርድ ሃላፊ ሆነው የተመረጡትን ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን በተመለከተ በገዢውም ሆነ በተቃዋሚ ፓርቲ እስካሁን ምንም የተሰማ ተቃውሞ የለም።

ሆኖም አንዳንድ ብሔርተኛ አክቲቪስቶች ወይዘሪት ብርቱካንን ለመሰየም የተጠራው የፓርላማ ቀን እንዲራዘም ጥያቄ አቅርበው ነበር።

የኢሕአደግ አባላት ሳይመክሩበት ተቃዋሚዎችም ሳይወያዩበት የተካሄደ ህገ-ወጥ ምርጫ ነው በሚል ተቃውመው እንደነበርም ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ትላንት በፓርላማ በሰጡት መግለጫ የወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ምርጫ በተመለከተ ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና ከአንጋፋ ዜጎች ጋር በመምከር የተደረሰበት ውሳኔ መሆኑን ገልጸዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም የጠቅላይ ሚኒስትሩን መግለጫ በማጠናከር በጉዳዩ ላይ ምክር ተጠይቀናል በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።

ዶክተር መረራ ጉዲና ከኦፌኮ፣አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት እንዲሁም አቶ የሽዋስ አሰፋ ከሰማያዊ ፓርቲ የወይዘሪት ብርቱካን ምርጫ በምክክር የተፈጸመና እነርሱም የተስማሙበት መሆኑን ለመንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

ቀጣዩ ምርጫ በተቀመጠለት መርሃ ግብር መሰረት ከቀጠለ ከአመት ከመንፈቅ በኋላ በግንቦት ወር 2012 ይካሄዳል።

በመንግስት በኩልም በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ምርጫው እንደሚካሄድ ተገልጿል።

ሆኖም ምርጫ ቦርድን አፍርሶ እንደገና በማዋቀር በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ምርጫ ማካሄድ አስቸጋሪ መሆኑ እየተገለጸ በብዙዎችም ዘንድ ስጋት እየተንጸባረቀ ይገኛል።

በተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይም ሕብረ ብሔር በሆኑት ሃይሎች ዘንድ በአመት ከ6 ወር ጊዜ ውስጥ ምርጫ ማካሄድ አስቸጋሪ መሆኑ በመግለጽ የመራዘሙ አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በዚህ ረገድ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአመት ከመንፈቅ ምርጫ ማካሄድ ከባድ መሆኑን ሲገልጹ የኦፌኮው ዶክተር መረራ ጉዲና ምርጫው የግድ መካሄድ ይኖርበታል ባይ ናቸው።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ አመራር አቶ አበበም በተመሳሳይ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ በዚህ ሁኔታ ምርጫ ውስጥ መግባት አደገኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በመንግስት መገናኛ ብዙሃን የቀረቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ደረጄ ዘለቀ መርጫውን የግዜ ገደብ ለማሟላት ብቻ ተብሎ ማካሄድ ተገቢ አይደለም ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የመራዘሙን ሒደትም አጽንኦት ሰጥተውበታል።