ከቤንሻንጉል ጉሙዝ የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ነው

ከቤንሻንጉል ጉሙዝ የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ነው
( ኢሳት ዜና መስከረም 24 ቀን 2011 ዓ/ም ) በቤንሻንጉል ጉሙዝ በካማሺና ሌሎችም ዞኖች የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር በእየለቱ እየጨመረ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት የተፈናቃዮች ቁጥር ከ150 ሺ በላይ መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል። መንግስት ያቋቋመው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አዲሱ ገብረ እግዚአብሄር መንግስት በቂ የመከላከል እርምጃ እንዳልወሰደ እና ግጭቱ መጨመሩን ሲገልጹ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ባለስልጣን ደግሞ ተፈናቃዮችን ለመርዳት ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ኢንሳይት ዛሬ ይዞት በወጣው ሰፊ ዘገባ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከካማሺ ዞን መፈናቀላቸውን ገልጿል።
አብዛኞቹ ተፈናቃዮች የኦሮሞና አማራ ተወላጆች ሲሆኑ፣ የካማሺ ዞን ባለስልጣናት መገደላቸውን ተከትሎ የጉሙዝ ወጣቶች በህዝቡ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ማቲዎስ ገለቲ የተባለ የከማሺ ዞን ነዋሪ ገልጿል።
የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት ከ75 ሺ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን እንደሚገልጹ የዘገበው ኢንሳይት፣ ትናንት ቢላላ ወረዳ የሚገኙ ወጣቶች ወደ ድንበር አካባቢ ለመሄድ ሲሞክሩ ፣ ብዙ ሰዎች መገደላቸውን፣ ብዙዎች መጥፋታቸውንና ንብረትም መውደሙን ስማቸውን እንዳይጠቀስ የፈለጉ ባለስልጣናን ጠቅሶ ዘግቧል። ከሁለት ቀናት በፊት ደግሞ ነጆ ከተማ ላይ ካለዲስ ናስር የተባለ ሰው መገደሉን አውስትራሊያ የሚኖርን ካህሊድ ናስር የተባለ አክቲቪስት በመጥቀስ ዘግቧል። ካሊድ የኦሮሞ ተወላጆች በፈጠሩት ጠብ አጫሪነት ግጭት መቀስቀሱን ተናግሯል።
ተፈሪ ዲዲሂታ የተባለ ቢላ ትምህርት ቤት ተጠልሎ የሚገኝ ወጣት በበኩሉ በካማሺ ወረዳ በሚርሚታ ቀበሌ 8 የኦሮሞ ተወላጆች መገደላቸውንና የጉሙዝ ወጣቶች የኦሮሞ ቤቶችን እየመረጡ ማጥቃታቸውን ገልጿል።
ከሳምንት በፊት የኦነግ ታጣቂዎች ለወሰዱት እርምጃ መንግስት አፋጣኝ መልስ እንዲሰጥ የአካባቢው ነዋሪዎች እየገለጹ መሆኑን ኢንሳይት ሲዘግብ ፣ ቶሌራ አዴባ የተባሉ የኦነግ ቃል አቀባይ፣ ኦነግ በግጭቶች እንዳልተሳተፈና መንግስትን ለማዳከም የሚንቃሳቀሱ ሃይሎች የኦነግን ስም ተጠቅመው የሚፈጽሙት ጥቃት መሆኑን ገልጻዋል። የቤንሻንጉል ጉሙዝ ነጻ አውጭ ድርጅት በበኩሉ ኦነግ በአካባቢው ተደጋጋሚ ጥቃት እየፈጸመ መሆኑን ገልጾ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች በኦሮሞዎች፣ አማራዎችና ትግሬዎች እየተጨቆኑ ነው ብሎአል።
በሌላ በኩል ደግሞ በካማሹ ዞን ተፈናቅለው በዞኑ የተለያዩ ወተረዳዎች 82 ሺ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የክልሉ የኦኮኖሚ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሙፍቲ መርቀኒ ለኢቲቪ ተናግረዋል። የእነዚህ ተፈናቃዮች አሀዝ ኦሮምያ ክልል ተፈናቅለው የገቡትን አያጠቃልልም። በአጠቃላይ ከክልሉ የተፈናቀሉ ሰዎችን ቁጥር ከ150 ሺ በላይ ደርሷል። እርዳታ ለመስጠትም ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑን አቶ ሙፍቲ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር አዲሱ ገብረ እግዚአብሄር ደግሞ ግጭቱ ዛሬም ድረስ የቀጠለ መሆኑን ገልጸዋል። ግጭቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ቢደርስም፣ መንግስት እና የጸጥታ ሃይሉ ግጭቱን ለመከላከል አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ አላደረጉም በማለትም ወቅሰዋል።
ጉዳዩ አሳሳቢ ቢሆንም፣ በመንግስት በኩል እስካሁን ይህ ነው የሚባል ጋዜጣዊ መግለጫ አልተሰጠም።