ከምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር ሸሽተው ሱዳን የገቡ ኢትዮጵያውያን ተመለሱ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 12/2011)በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር በተከሰቱ ግጭቶች ሽሽተው ሱዳን ከገቡ ኢትዮጵያውያን መካከል 1500 የሚሆኑትን ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ ማድረጉን የመከላከያ ሰራዊት አስታወቀ።

የሰራዊቱ 33ኛ ብርጌድ እንዳስታወቀው በቅርቡ በአካባቢዎቹ ተከስተው የነበሩትን ግጭቶች ተከትሎ ወደ ሱዳን የገቡ ኢትዮጵያውያንን ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ የማድረጉ ስራ እየተካሄደ ነው።

የብርጌዱ አዛዥ ብርጋዲየር ጄነራል ዓለሙ አየለ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ሌሎች ኢትዮጵያውያንንም ለማስመለስ ሰራዊቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ ነው።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር የተከሰቱት ግጭቶች በመቶዎች ለሚቆጠር ህይወት መጥፋት ምክንያቶች ነበሩ።

ቤቶች ተቃጥለዋል፣ ንብረቶች ወድመዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል።

የተፈናቀሉት ነዋሪዎች ደግሞ ሽሽታቸው በሀገር ውስጥ ብቻ የቆመ አልነበረም።

ድንበር አቋርጠው ሱዳን የገቡት ቁጥራቸው በውል ባይታወቅም በርካቶች አጎራባች የሱዳን ግዛቶች ውስጥ መግባታቸው መዘገቡ የሚታወስ ነው።

በሱዳን ገለባትና ገዳሪፍ በሚገኙ የመጠለያ ጣቢያዎች የቆዩት ተፈናቃይ ነዋሪዎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳሉ በመግለጽ መንግስት እንዲደርስላቸው በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ምንም እንኳን ግጭቶቹ በተከሰቱባቸው አካባቢዎች እርቀሰላም በማውረድ ሰላም እንዲፈጠር የተደረገ ቢሆንም ሀገር ጥለው የተሰደዱ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ሳይደረግ መቆየቱ አብዛኞቹን ተፈናቃዮች ለከፋ ችግር መዳረጉን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።

የመከላከያ ሰራዊት የ33ኛ ብርጌድ መምሪያ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቀው ግን ሰሞኑን በሁለቱ ሃገራት ትብብር በተደረገ ጥረት 1500 ተፈናቃዮችን ከገለባትና ገዳሪፍ እንዲመለሱ ተደርገዋል።

የብርጌድ አዛዡ ብርጋዴር ጄነራል አለሙ አየለ እንደገለጹት በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ የሚገኙ ሰራዊቶች ያቋቋሙት ጥምር ኮሚቴ በወሰደው የማስመለስ ርምጃ አብዛኛው ተፈናቃይ ወደ ሀገሩ ገብቷል።

አሁን የቀሩት ጥቂት መሆናቸውን የገለጹት ብርጋዴር ጄኔራል ዓለሙ እነዚህን በሚቀጥሉት ቀናት ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰው በቀያቸው የቀድሞ ኑሯቸውን እንዲጀምሩ የሚደረጉ ይሆናል ብለዋል።

በአጠቃላይ ምን ያህል ኢትዮጵያውያን በግጭቶቹ ምክንያት ወደ ሱዳን ሸሽተው እንደገቡ የታወቀ ነገር ባይኖርም ሁሉንም የመመለሱ ተግባር እንደሚከናወን ነው 33ኛ ብርጌድ መምሪያ ያስታወቀው።

አዛዡ ብርጋዴር ጄነራል ዓለሙ አየለ ጨምረው እንደገለጹት በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር ተፈጥረው በነበሩ ግጭቶች ምክንያት ተቋርጦ የነዳጅና የተለያዩ ምርቶች የማዘዋወሩ የትራንፖርት እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

አካባቢውን የበለጠ ሰላማዊ ለማደረግ የብርጌድ መምሪያው እየሰራ ነው ብለዋል አዛዡ።

በኢትዮጵያ ከመፈናቀል ጋር በተያያዘ የመንግስት ሃላፊዎች እጃቸው እንዳለበት የሰላም ሚኒስትሯ በቅርቡ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

ለፖለቲካና ለኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸው ሲሉ ማፈናቀል እንዲፈጸምና ከተፈጸመም በኋላ ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው እንዳይመለሱ በማድረግ የመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት እንደሚገኙበት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፍሪያት ካሚል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልጸዋል።

እነዚህን ባለስልጣናት ጨምሮ ከ1ሺህ በላይ ሰዎችን በቁጥጥር ስር በማድረግ ምርመራ መጀመሩን መንግስት አስታውቋል።