ከምንም ጊዜ በላይ ዛሬ ለእውነት የምንቆምበት ጊዜ ላይ ነን ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 17/2011) ከምንም ጊዜ በላይ ዛሬ ለእውነት የምንቆምበት ጊዜ ላይ ነን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ገለጹ።
“የሐሰት ወሬዎች፣ አሳሳች አሉባልታዎች በስሜት የሚነዱ ማስመሰሎች በገፍ አሉ”በማለት የመስቀልን በአል በማስመልከት መልዕክት ያስተላለፉት ዶክተር አብይ አሕመድ እንደደመራ ችቦ ተደምረን መቆም አለብን ሲሉም ጥሪ አስተላልፈዋል።

“ችቦዎች ብቻቸውን ደመራ አይመሰርቱም፣አንድ ላይ ሆነው በአንድ ዋልታ ዙሪያ መቆም አለባቸው ይህ ዋልታም ኢትዮጵያዊነታችን ነው “ብለዋል ዶክተር አብይ አህመድ የመስቀል በአልን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ።
“ሁላችንም የምንቆምበትና የምንቆምለት ሐገራዊ እሴትና ማንነት ሃገራዊ አንድነትና ሃገራዊ መንግስት አለን።ያንን ለመፍጠር ነው ሁላችንም አንድ ላይ ተደምረን የምንቆመው’’ሲሉም አክለዋል።
እውነትን በውሸትና በተንኮል፣በቅጥፈትና በሴራ፣በየትኛውም የስልጣን ደረጃ በዘላቂነት ሸፍኖ መኖር እንደማይቻል የክርስቶስ መስቀል ታሪክ ግሩም ማስረገጫ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በመግለጫቸው።
በጊዜያዊ ጥቅምና በስልጣን እውነትን ለጊዜው ብንቀብራት እውነት ግን እውነት ናትና ግዜዋን ጠብቃ መውጣቷ ብቻ ሳይሆን በተለየ በድንቅ የመገለጥ ሚስጥር ትነሳለች ሲሉ ተናግረዋል።
በሐሰት መሪዎች፣በአሳሳች አሉባልታዎችና በማስመሰል ከግርግር ባሻገር ዘላቂ ድል አይገኝም ያሉት ዶክተር አብይ አህመድ “እኛ መከራን፣ችግርን፣ጦርነትና ግጭትን በበቂ ሁኔታ ቀምሰናቸዋል፣አይናፍቁንም፣አንመኛቸውም ተደምረናልና ከእንግዲህም የእንባ ሰበቦቻችን አይቀጥሉም፣እንዲቀጥሉም አንፈቅድም” ብለዋል።
በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ሊፍጨረጨሩ የሚችሉ ቢኖሩም ይህም ከመስቀል በኋላ እንደሚመጣ ዝናብ የማይዘልቅ መሆኑን አመልክተዋል።
ይህ እውን እንዲሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።