ኦዴፓ በዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ምትክ አቶ ኡመር ሁሴንን የስራ አስፈፃሚ አባል አደረገ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት19/2011) የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ማእከላዊ ኮሚቴ በዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ምትክ አቶ ኡመር ሁሴንን የስራ አስፈፃሚ አባል አድርጎ መረጠ።

የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለሶስት ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን ስብሰባውን  አጠናቋል።

የኦዴፓ ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር አለሙ ስሜ  በሰጡት መግለጫ የማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባው የተለያዩ ውሳኔዎችንና ምትክ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል በመምረጥ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

በዚህም መሰረት የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ከፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት በለቀቁት ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ምትክ አቶ ኡመር ሁሴንን የስራ አስፈፃሚ አባል አድርጎ መምረጡን አስታውቀዋል።

በዚሁ መሰረት የኦዴፓ ስራ አስፈፃሚ አባላትም ዶክተር አብይ አህመድ አቶ ለማ መገርሳ አቶ ኡመር ሁሴን ዶክተር አለሙ ስሜ አቶ ሽመልስ አብዲሳ አቶ አዲሱ አረጋ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አቶ ፍቃዱ ተሰማ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ መሆናቸውን የፅህፈት ቤት ሀላፊው በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በቅርቡ ኬኒያ ለሚገኘው ቢሮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ጸሀፊ ሆነው መሾማቸው ይታወሳል።

ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ መቀመጫውን ኬንያ ናይሮቢ ያደረገውን የተመድ ዋና ጽህፈት ቤት የመምራት እና የማስተባበር ሃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።