ኦነግ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም አወጀ

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 5/2010) የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም አወጀ።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና በኦነግ ሊቀመንበር በአቶ ዳውድ ኢብሳ መካከል የተደረገው ንግግር ለርምጃው ምክንያት እንደሆነም ተመልክቷል።

ኦነግ ለግንባሩ ሰራዊት ውሳኔውን ተግባራዊ እንዲያደርግም መመሪያ አስተላልፏል።

“የተጀመረውን የሰላም ውይይት ለማሳካት በኦሮሞ ነጻነት ግንባር የታወጀ ጊዜያዊ የተኩስ ማቆም መግለጫ” በሚል ርዕስ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ባወጣው መግለጫ፣ ለረዥም ዓመታት ችግሩ በሰላም እንዲፈታ ሲያደርግ የነበረውን ጥረት አስታውሷል።

በመንግስት በኩል ለሰላሙ ጥሪ ቀና ምላሽ እንዳልነበር የጠቀሰው ኦነግ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በተደረገ ንግግር በሂደቱ አንድ ርምጃ መጓዙን ገልጿል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የተጀመረውን የሰላም ንግግር ከደረሰበት ወደ ፊት ለማራመድና ለማሳካት በሚል ለጊዜው ተኩስ ማቆሙን አስታውቋል።

ይህ ጊዜያዊ ተኩስ ማቆም ፍሬ አፍርቶ አጠቃላይ ጦርነት ወደ ማቆም አዋጅ እንደሚሸጋገርም ያለውን ዕምነት ገልጿል።

ሰራዊቱም ይህን መመሪያ እንዲያከብር ጥሪ አቅርቧል።