ኦነግ የአካባቢውን ሰላም እያደፈረሰ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 26/2011)የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ከመንግስት ጋር የደረሰውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ባለመተግበሩ  የአካባቢው ሰላም እየደፈረሰ መሆኑን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

የኦነግ ለሰላም አለመገዛት ሊሰብሩን የሚፈልጉ ሃይሎች ፍላጎትን ለማሳካት በሚችል መልኩ የኦሮሚያ ክልልን ሰላም አደፍርሷል ብሏል መግለጫው።

በተለይም በአራቱ የወለጋ ዞኖች እና በምእራብ ጉጂ ዞን በየእለቱ የሰው ህይወት እያለፈና ንብረት እየወደመ መሆኑን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ገልጿል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በአራቱ የወለጋ ዞኖች እና በምዕራብ ጉጂ ዞን መንገዶች በመዘጋታቸው የንግድ እንቅስቃሴ መቆሙን አስታውቋል።

እናም ህዝቡ ለከፍተኛ ችግር እየተጋለጠ መሆኑን ነው የገለጸው።በአካባቢዎቹ በየእለቱ የሰው ህይወት እያለፈና ንብረት እየወደመ ነውም ብሏል።

ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸውም የኦሮሞ ህዝብ ከጨለማ ወደ ብርሃን መውጣት በጀመረበት በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ህጻናት መሃይምነት ውስጥ እንዲቆዩ እያተደረገ ነው ሲልም ምሬቱን ገልጿል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በመግለጫው እንዳለው የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት አገልግሎት መስጠት በማቆማቸውም ወላድ እናት በመንገድ ላይ ህይወቷ እያለፈ ይገኛል።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ከመንግስት ጋር የደረሰውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ባለመተግበሩ ትናንት ሊሰብሩን የሚፈልጉ ሀይሎች ፍላጎትን ለማሳካት በሚችል መልኩ የኦሮሚያ ክልል ሰላም እየደፈረሰ መሆኑንም ገልጿል።

ሰላማዊ ህዝብ ውስጥ በመንቀሳቀስ አደጋ ማድረስ፣ ለህዝቡ የቆመን የፀጥታ ሃይል መግደል፣ የጦር መሳሪያ በመዝረፍ ሁከት መፍጠር የተለመደ የወንጀል ድርጊት መሆኑንም ገልጿል።

ኦሮሚያን የጦርነት አውድማ ለማድረግ “ኦሮሞ ሀገር መምራት አይችልም፥ የሽግግር መንግስት ነው የሚያስፈልገው” ማለት የተጀመረውን ለውጥ ያደናቅፋል አንጂ አያሻግርም ብሏል።

የውሃና የመንገድ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ቆመዋል፣ የንግድ እንቅስቃሴም በመቆሙ ህዝቡ ለከፍተኛ ችግር ከመጋለጥም አልፎ የፀጥታ ስጋት ውስጥ ገብቷልም ብሏል።

የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያወጣው መግለጫ እንዳመለከተው የህግ የበላይነት ተከብሮ ሰላም እንዲረጋገጥ የህዝቡ ተሳትፎ መጠናከር ይኖርበታል።

ስልጣን ከእጃቸው የወጣ አካላት በየስፍራው ሴራ በመሸረብ አሁን የተጀመረው ለውጥ እንዲደናቀፍ ሌት ተቀን እየሰሩ መሆኑንም አስታውቋል።

እናም መንግስት ግዳጅ ስላለበት የህግ የበላይነት ተከብሮ ሰላም እንዲሰፍን እየሰራ መሆኑን ነው የገለጸው።

ለዚህም ህዝቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጥሪ አስተላልፏል።