ኦነግ በሰኔ 16ቱ የቦምብ ጥቃት እጄ የለበትም አለ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 8/2011)በአዲስ አበባ ከተማ ሰኔ 16/2010 በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ላይ በተቃጣው የግድያ ሙከራ እጁ እንደሌለበት ኦነግ ገለጸ።

ኬንያ ሆና ድርጊቱን በማቀነባበር የተጠረጠረችው ግለሰብ አባላችንም ሆነ ደጋፊያችን አይደለችም ሲሉ የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ተናግረዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ/ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከ25 አመታት በፊት በበደኖ ከተማ በኦነግ ተፈጸመ የተባለውን አሰቃቂ ግድያ አስተባብለዋል።

ገለልተኛ መርማሪ አካል እንዲቋቋም ያኔም ጥያቄ ማቅረባቸውንም ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል አስታውቀዋል።

ሰኔ 16 ቀን 2010 መስቀል አደባባይ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በተጠራ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ጥቃት ያደረሱት ወገኖች በኦነግ የሚመራ መንግስት እንዲመሰረት እንደሚፈልጉ በአቃቤ ህግ ክስ ላይ መገለጹ ይታወሳል።

ድርጊቱን ከኬንያ ናይሮቢ ያቀነባበረችው ገነት ታምሩ ወይንም ቶሎሺ ታምሩ የተባለች ግለሰብ እንደሆነችም ተመልክቷል።

በዚህ ጥቃት እጃችን የለበትም ያሉትና መንግስትም በቀጥታ ድርጊቱን ኦነግ ፈጽሟል አላለም ያሉት አቶ ዳውድ ኢብሳ ገነት የምትባለውን ሰው ድርጅታቸው እንደማያውቃትም ገልጸዋል።

ምናልባት ደጋፊ ትሆን ወይ?በሚል ባደረግነው ማጣራትም አባልም፣ደጋፊም እንዳልሆነች አረጋግጠናል ብለዋል።

በመስከረም ወር መጀመሪያ በቡራዩ ከተፈጸመው ግድያ ጋር በተያያዘም ኦነግ እጁ የለበትም ያሉት አቶ ዳውድ ኢብሳ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተገደሉትን 4 የቤንሻንጉል ክልል ባለስልጣናት በተመለከተ ምርመራ እናደርጋለን ብለዋል።

ሆኖም በዚህ ሳቢያ በንጹሃን ላይ የተፈጸመው የአጸፋ ጥቃት ተቀባይነት እንደሌለውም አመልክተዋል።

ከ25 አመታት በፊት በበደኖ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ ኦነግ አልፈጸመም በማለት ያስተባበሉት የኦነጉ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ያኔም ገለልተኛ አካል እንዲመረመር ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሰዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ትጥቅ ስለመፍታቱ ተጠይቀውም “ትጥቅ ፈቱ መባል አንፈልግም፣ይህ አባባል አንዱ አስፈቺ ሌላው ፈቺ ያስመስለዋል” ብለዋል።