ኦነግ በምዕራብ ኦሮሚያ ጦርነት ተከፈተብኝ አለ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 30/2011) የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ በምዕራብ ኦሮሚያ ጦርነት እንደተከፈተበት ገለጸ።

ሶስተኛ ወገን ባለበት ከመንግስት ጋር ለመደራደር ያለውንም ዝግጅት ገልጿል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ “ሰላም ይሰፍን ዘንድ ጦርነቱ ቆሞ ስምምነታችን ሊታደስና ሊጠናከር ይገባል” በሚል ርዕስ ትላንት ታህሳስ 29/2011 ባወጣው መግለጫ ኢህአዴግ ከኦነግ ጋር የደረሱበትን ስምምነት በመጣስ በኦሮሚያ ክልል በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ ጦርነት እንደተከፈተበት ገልጿል።

ኢህአዴግና በርሱ የሚመራው መንግስት ከጸረ-ዲሞክራሲ አቋማቸው ፈቅ ማለት አልቻሉም ያለው በአቶ ዳወድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ ወደ ሃገር ቤት ከገባበት ግዜ ጀምሮ እንቅፋቶች ሲፈጠሩበት መቆየታቸውን ገልጿል።

ኦነግ በመጨረሻም ሁሉም ወገኖች በተለይም የኦሮሞ ህዝብ መንግስት ላይ ጫና እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

ሶስተኛ ወገን ባለበት ከመንግስት ጋር ለመደራደር ፍላጎቱ መሆኑንም በመግለጫው አመልክቷል።