ኤርትራ በአፋር በኩል ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር ዘጋች

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 14/2011)ኤርትራ በአፋር በኩል ከኢትዮጵያ የሚያዋስናትን ድንበር መዝጋቷ ታወቀ።

ወደ ኤርትራ የሚያስገባው የቡሬ መስመር ከትላንት ጀምሮ መዘጋቱን የአፋር ክልላዊ መንግስት አስታውቋል።

ፋይል

ኤርትራ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር ስትዘጋ የቡሬው ሁለተኛው መሆኑ ነው።

ባለፈው ሳምንትም በሁመራ መስመር ያለውን ድንበሯን መዝጋቷ የሚታወስ ነው። የቡሬ መስመር የተዘጋበት ምክንያት ግን አልተገለጸም።

የትላንቱ የቡሬው መስመር መዘጋቱን ተከትሎ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስኗትን ሶስቱን ድንበሮቿን በሙሉ መዝጋቷ ነው የተረጋገጠው።

የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በተገኙበት ባለፈው ታህሳስ ወር የተከፈተውና ከቡሬ ወደ አሰብ የሚወስደው መስመር በትላንትናው ዕለት መዘጋቱን የገለጹት የአፋር ክልል አመራሮች ምክንያቱን ግን እንደማያውቁት ነው የተናገሩት።

ባለፈው ሳምንት ኤርትራ በሱዳን ከሚያዋስናት የኡምናሀጅር ድንበር ላይ ሰራዊቷን ማስፈሯን ተከትሎ የሁመራውን መስመር እንዲዘጋ ማድረጓ የሚታወስ ነው። በተመሳሳይ በዛላምበሳ በኩል ያለውን የድንበር ከተሞቿን በሙሉ ከኢትዮጵያ ለሚገቡ ማናቸውም ተሽከርካሪዎች ሆነ የሰው ዝውውር ዝግ ማድረጓ ይታወቃል።

ኤርትራ በሁኑ ጊዜ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስኗትን የድንበር መስመሮች በሙሉ መዝጋቷ ከምን የመነጨ እንደሆነ በሁለቱም ሀገራት በኩል የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ የለም።

ኢሳት ከሁለቱም መንግስታት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

በዛላምበሳና በቡሬ በኩል ያሉትን ድንበሮች በተመለከተ አንዳንድ የመረጃ ምንጮች ከህገወጥ የንግድ ዝውውር ጋር ያያይዙታል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል የንግድና ሌሎች ግንኙነቶችን የተመለከቱ ስምምነቶች ከመደረሳቸው በፊት በህገወጥ መንገድ የሚደረገው የንግድ እንቅስቃሴ ድንበሮቹ እንዲዘጉ ማድረጋቸውን የሚገልጹት ወገኖች ህጋዊ መስመር እስኪያዝ እንጂ መከፈታቸው አይቀርም ሲሉ ይናገራሉ።

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ጉዳዩን ከጸጥታ ጋር በማያያዝ ይገልጹታል።

ድንበሮቹ መከፈታቸውን ተከትሎ ኤርትራ ለደህንነቷ የሚያሰጉ ፣ምልክቶችን ማየቷን የሚጠቅሱት ምሁሩ በተለይም ከህወሃት በኩል የኤርትራን ሰላም የማወክ ፍላጎትን በቀላሉ የሚያሳካ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት በኤርትራ በኩል ይኖራል በማለት ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

ባለፈው ሳምንት በኡምናሀጅር በኩል ኤርትራ ድንበሯን ስትዘጋ በቀጥታ ከሱዳን ጋር ባላት ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት ጋር የተያያዘ መሆኑን የኤርትራ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

የዛላምበሳና ቡሬ ድንበሮችን በተመለከተ በኤርትራ መገናኝ ብዙሃን በኩል የተሰጠ ምክንያት የለም።

ሁለቱ ሀገራት ከ20 ዓመታት ጥይት አልባ ጦርነት በኋላ ታሪካዊ በተባለ ስምምነት ወደ ሰላም የመጡት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ሲሆን የሁለቱም ሀገራት መሪዎች አዲስ አበባና አስመራ በተደጋጋሚ በመገናኘት በቀጠናው አዲስ ምዕራፍ መጀመራቸው ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትና ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል።