ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ የሞ ኢብራሔም ፋውንዴሽንን ሽልማት አሸነፉ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 5/2010)

የቀድሞዋ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ የሞኢብራሔም ፋውንዴሽንን የ5 ሚሊየን ዶላር የመሪነት ሽልማት አሸነፉ።

በአለም ላይ ከፍተኛ የሆነውንና ከኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች የበለጠ የገንዘብ ስጦታ የሚያስገኘውን የአፍሪካ የመሪነት ሽልማት ከሞኢብራሒም ፋውንዴሽን በማግኘት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ 5ኛ ሆነዋል።

ሰርሊፍ የመጀመሪያዋ በምርጫ ስልጣን የያዙ እንስት የአፍሪካ መሪ መሆናቸውም ይታወቃል።

በባለጸጋው ሙሐመድ ኢብራሒም የሚመራው የሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን የሽልማት ኮሚቴ ላለፉት 2 አመታት ለሽልማቱ የሚበቃ የአፍሪካ መሪ ባለማግኘቱ የ5 ሚሊየን ዶላሩን ሽልማት ሳይሰጥ ቆይቷል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2017 ለዚህ ሽልማት ብቁ ሆነው የተገኙት የ79 አመቷ የቀድሞ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2006 በላይቤሪያ በምርጫ አሸንፈው ስልጣን ይዘዋል።

በ2018 በሀገራቸው በተካሄደው ምርጫም አሸናፊ ለሆነው ለታዋቂው የእግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃ ስልጣናቸውን በሰላማዊ መንገድ አስረክበዋል።

የሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን ሽልማት ኮሚቴ ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ሙስናን በመዋጋት ረገድ ደካማ መሆናቸውን አስታውቋል።

ሆኖም ሀገሪቱ ከእርስ በርስ ጦርነቱ እንድታገግም በማድረጋቸው እንዲሁም የዕርቅ መንፈስ በማስፈናቸው በአጠቃላይ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የመሪነት ብቃታቸውን በማሳየታቸው የ2017 የሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን አሸናፊ መሆናቸውን ይፋ አድርጓል።

ኤለን ጆንሰን ሰር ሊፍ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2011 ከላይቤሪያዊቷ የሴቶች መብት ተሟጋች ሊማ ጊቢዊና ከየመኗ ጋዜጠኛና የመብት ተሟጋች ታሞኮል ካርማን ጋር በጋራ የሰላም የኖቤል ሽልማት ማግኘታቸው ይታወሳል።

በትውልድ ሱዳናዊ በዜግነት እንግሊዛዊ በሆኑት ባለጸጋ ሙሐመድ ኢብራሒም ባለቤትነት የሚመራው የሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን ይህንን በአለም ላይ ከፍተኛ የሆነውን ሽልማት ለመጀመሪያ ጊዜ ለሞዛምቢኩ የቀድሞ መሪ ጃኦኪም ቺሳኖ እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2007 የሰጠ ሲሆን በ2008 ደግሞ ለቦትስዋና የቀድሞ ፕሬዝዳንት ፌስተስ ሞጌ አበርክተዋል።

በ2009ና በ2010 ለሽልማቱ የሚበቃ አፍሪካዊ መሪ በመታጣቱ የታለፈ ሲሆን በ2011 የኬፕቨርዲው የቀድሞ መሪ ፔድሮ ቬሮና ፒርስ ተሸልመዋል።

በ2012ና በ2013 ለሽልማቱ የሚመጥን የአፍሪካ መሪ በመታጣቱ በ2014 የቀድሞው የናሚቢያ መሪ ሒፍኪፑኒ ፎአምባ የ5 ሚሊየን ዶላሩን ሽልማት ተቀብለዋል።

በ2015ና በ2016 ለዚህ ከፍተኛ ሽልማት የሚበቃ የአፍሪካ መሪ የሽልማት ኮሚቴው ባለማግኘቱ የላይቤሪያ የቀድሞ መሪን ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍን የ2017 አሸናፊ አድርጓቸዋል።

የሞ ኢብራሒም የመሪነት ሽልማት 5 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን ይህም በ10 አመታት ተከፋፍሎ የሚሰጥ ነው።

ከ10 አመታት በኋላ ደግሞ እስከ እድሜ ልክ በአመት 200 ሺ ዶላር ለአሸናፊው እንደሚሰጥም መረዳት ተችሏል።