ኢንተርኔት መዘጋቱን ተከትሎ የመንግስትና የፓርቲ የመገናኛ ብዙሃን ሳይቀሩ ዜናዎችን ማውጣት አቆሙ

ግንቦት ፳፭ ( ሃያ አምስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ የተዘጋውን የኢንትርኔት አገልግሎት ተከትሎ የውጩን ማህበረሰብ ስለአገሪቱና ስለመንግስቱ መልካም ገጽታ እንዲኖረው በሚል ዘገባዎችን የሚያቀርቡ የመንግስት ሚዲያዎች፣ የፓርቲ ሚዲያዎችና በፌስቡክ፣ በቲውተርና በድረገጻቸው የገዢውን ፓርቲ አወንታዊ ገጽታ ሲያቀርቡ የነበሩ ሁሉ እንቅስቃሴ አቁመዋል።
የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ከሆኑት መካከል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኤጀንሲ የኢንተርኔት ገጻቸው የተዘጋ ሲሆን፣ የህወሃት ንብረት የሆኑት ሬዲዮ ፋናና ዋልታ ኢንፎረሜሽን ማእከል ደግሞ ዜናዎችን ማቅረብ ካቆሙ 3ኛ ቀን ተቆጥሯል። ገዢው ፓርቲ አሰልጥኖ የተለያዩ ቅስቀሳዎችን በፌስቡክ እና በትዊተር የሚያደርጉትም እንዲሁ ስራቸውን ካቆሙ 3 ቀናት ሞልቷል።
በግል ከተቋቋሙት ሚዲያዎች መካከል ሸገር ሬዲዮ የተባለው የሬዲዮ ጣቢያም እንዲሁ የኢንተርኔት ስርጭቱ ተቋርጧል።
ሌሎች በኢንተርኔት ዘገባዎችን የሚያውጡ የመገናኛ ብዙሃንም እንዲሁ ስራቸው ተቋርጧል። የኢንተርኔት መቋረጡ ብሄራዊ ፈተናን ከስርቆት ለመካለከል በሚል የተወሰደ እርምጃ መሆኑን የአገዛዙ ባለስልጣን ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል ግን ውሳኔው በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽኖ እያመጣ ነው። በተለይ የንግድ ባንኮች ስራቸውን በተገቢው መንገድ መስራት አልቻሉም። ለገጽታ ግንባታ ከፍተኛ ገንዘብ መድቦ የሚንቀሳቀሰው አገዛዙ፣ የራሱን አባላት ጭምር አፍኗል። የአለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃንም ውሳኔውን ፖለቲካዊ ገጽታ ሰጥተው እየዘገቡት ነው።