ኢትዮጵያ የባህር ሃይል ጣቢያ ልትገነባ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 29/2011) ኢትዮጵያ የባህር ሃይል ጣቢያ ልትገነባ መሆኗን አስታወቀች።

በሐገር መከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ምክትል ኤታማዦር ሹምና የዘመቻ መምሪያ ዋና ሃላፊ ጄነራል ብርሃኑ ጁላ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በቀይባህርና ህንድ ውቅያኖስ አቅራቢያ የባህር ሃይል ሰፈር ልትገነባ በዝግጅት ላይ ናት።

በአፍሪካ ትልቅና ጠንካራ የባህር ሃይል የነበራት ኢትዮጵያ የህወሃት አገዛዝ ወደ ስልጣን መምጣቱን ተከትሎ ባህር ሃይሏ መፍረሱ የሚታወስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ የባህር ሃይል እንዲኖራት ውሳኔ ላይ በመድረሳቸው እንቅስቃሴው መጀመሩን የገለጹት ጄነራል ብርሃኑ ጁላ በቀጠናው እየተጠናከረ የመጣውን የሌሎች ሀገራት ፍላጎት በቅርበት እየተከታተልን ነው ብለዋል።

ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ቃለመጠይቅ የሰጡት ምክትል ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ኢትዮጵያ ከ27 ዓመታት በኋላ የባህር ሃይል ተቋም ሊኖራት በዝግጅት ላይ መሆኗን ገልጸዋል።

በጥንካሬውና ተቋማዊ ቅርጹ ከአፍሪካ ቀዳሚ ባህር ሃይል የነበራት ኢትዮጵያ የመንግስት ለውጥን ተከትሎ የባህር በር በማጣቷ ከሩብ ክፍለዘመን በላይ የባህር ሃይል ሳይኖራት ቆይቷል።

ጄነራል ጁላ ለኢዜአ እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ ጠንካራና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የዳበረ የባህር ሃይል እንዲኖራት ራዕይ ያላቸው በመሆኑ ይህን ወደ እውነት ለመቀየር በመንግስት በኩል ውሳኔ ላይ ተደርሶ ዝግጅት እየተደረገ ነው።

ትልቅ ሀገር የሆነችውና ጠንካራ የጦር ሰራዊት አቅም ያላት ሀገር የባህር ሃይል ሊኖራት ይገባል የሚል ጠንካራ አቋም በመንግስት ደረጃ ተይዟል ነው ያሉት ጄኔራል ብርሃኑ።

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ የባህር በር ባኖራትም በህንድ ውቅያኖስና በቀይ ባህር አቅራቢያ በሚገኝ ስፍራ የኢትዮጵያን የባህር ሃይል ቤዝ ለማቋቋም መታቀዱን ጄኔራል ብርሃኑ ገልጸዋል።

ለውጭ ንግድ ማስገቢያና ማስወጪያ የምትጠቀመውን የቀይባህር የወደብ አገልግሎት ታሳቢ በማድረግ በዚያው የባህር ሃይል ተቋም መገንባቱ ኢትዮጵያን በተለያዩ መስኮች የሚጠቅም ሆኖ ተግኝቷል ያሉት ጄነራሉ፡ በርካታ ሃገራት በአፍሪካው ቀንድ የወታደራዊ ጣቢያ የማቋቋም ፍላጎት እያሳዩ በመሆናቸው ኢትዮጵያም የራሷን መገንባት ይገባታል ሲሉ ገልጸዋል።

በሶማሌላንድ ጅቡቲ፣ ፑንትላንድና ኤርትራ የወደብ አካባቢዎች ታላላቅ ሃብታም ሃገራትን ጨምሮ አረቦቹ በስፋት እየገቡ መሆናቸውን በመጥቀስ የኢትዮጵያ የባህር ሃይል ጣቢያ በቀይባህርና ህንድ ውቅያኖስ አካባቢ በስልሳ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ለመገንባት እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብለዋል ጄነራል ብርሃኑ ጁላ።

በአሁኑ ጊዜ በባህር ሃይል ዘርፍ ላቅ ያለ ደረጃ የደረሱ ሀገራትን በማማከር ላይ ነን ያሉት ጄነራል ብርሃኑ ኢትዮጵያን ከውጭ ሃይሎች ጥቃት መመከት በሚያስችል ወታደራዊና ሳይንሳዊ አቅም የሚገነባ ባህር ሃይል ይኖረናል በማለት ገልጸዋል።