ኢትዮጵያ የሶማሊላንድን ወደብ ለመጠቀም ድርድር እያካሄደች ነው ተባለ

ኢሳት (ሰኔ 2 ፥ 2009)

ኢትዮጵያ የሶማሊላንድ ወደብን ለመጠቀም የሚያስችል አዲስ ድርድር ወደቡን ከተረከበው የዱባይ ኩባንያ ጋር መጀመሯን የሶማሊያ ከፊል ራስ ገዝ አስተዳደር የሆነችው የሶማሊላንድ ባለስልጣናት አስታወቁ።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ወደቡን በጋራ ለማልማት ከሶማሊላንድ ጋር ረጅም ጊዜ የፈጀ ድርድርን ብታካሄድም ስምምነት ሳይደረስ መቅረቱ ይታወሳል።

ከኢትዮጵያ ጋር የተጀመረው ድርድር ዕልባት አለማግኘቱን ተከትሎ የሶማሊላንድ ባለስልጣናት ወደቡን ዲፒ ወርልድ ለተሰኘ የዱባይ ኩባንያ አስረክበዋል።

ከወራት በፊት የበርበራን ወደብ ለማልማትና ከሶማሊላንድ ጋር በጋራ ለመጠቀም ስምምነት የደረሰው ኩባንያው ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ በመመደብ የወደቡን 51 በመቶ ድርሻ መያዙን ብሉምበርግ አርብ ዘግቧል።

የሶማሊላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳድ አሊሺሬ የኢትዮጵያ መንግስት 19 በመቶ ድርሻን ለማግኘት ድርድር መጀመሩን አስታውቀዋል።

በጅቡቲ ወደብ ላይ የወጪና ገቢ ንግዷን ጥገኛ አድርጋ የምትገኘው ኢትዮጵያ ለወደብ አገልግሎት ብቻ በአመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንደምታደርግ ታውቋል።

ኢትዮጵያ አማራጭ የወደብ አገልግሎትን ለማግኘት ፊቷን ወደ ሶማሊላንድ ብታዞርም የጅቡት ወደብን የሚያስተዳደረው ዲፖ ወርልድ ኩባንያ የሶማሊላንድ ወደብ በአብላጫ ባለቤትነት ይዞ የሚገኝ በመሆኑ ሃገሪቱ አሁንም አጣብቂኝ ውስጥ መሆኗ ይነገራል።

ኢትዮጵያ አዲስ ስለጀመረችው ድርድር መረጃ እንድትሰጥ ብትጠየቅም፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ ሳይሰጥ መቅረቱን ብሉም በርግ በዘገባው አመልክቷል።

የሶማሊላንድ ባለስልጣናት ኢትዮጵያ ሽርክናን ለማግኘት የጀመረችው ድርድር እስካሁን ድረስ ህጋዊ ውሳኔን እንዳላገኘ አክለው አስረድተዋል።

በ40 ሃገራት ተመሳሳይ ወደቦችን እያስተዳደረ የሚገኘው የዱባዩ ኩባንያ የወደቡ የሽርክና ይዞታው 65 በመቶ አካባቢ ሊደርስ እንደሚችል የሶማሊላንዱ ውጭ ጉዳይ ሚኒቴር ለዜና አውታሩ ገልጿል።

ይኸው ኩባንያ የበርበራ ወደብን ለ30 አመት ለማስተዳደር ስምምነት የደረሰ ሲሆን፣ በተመሳሳይ መልኩ የጅቡቲ ወደብን ለ50 አመት መረከቡንም ብሉምበርግ የዜና ወኪል በዘገባው አመልክቷል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር በርበራ ወደብ ሽርክናን ለማግኘት የሚታደርገው ድርድር ሶማሊላንድ እንደ ሃገር የመቀበል ጉዳይ አይደለም ሲሉ የመንግስት አካላት መግለጻቸው ተመልክቷል።

ሶማሊላንድ ራሷን እንደ ነጻ ሃገር አድርጋ ብታወጅም እስከአሁን ድረስ እንደ ሃገር የተቀበላት አካል የሌለ ሲሆን፣ የሶማሊላንድ መንግስት ከግዛቲቱ ጋር የሚደረግን ስምምነት በቅርበት እንደሚከታተለው ለመረዳት ተችሏል።

የተባበሩት አረብ ኤመሬትስ በሶማሊላንድ ወታደራዊ ማዘዥ ጣቢያን ለማቋቋም ስምምነት መድረሷን ሲገለጽ ቆይቷል።

ይሁንና የሶማሊያ መንግስት ዕርምጃው ህገወጥ ነው በማለት ተቃውሞን አቅርቧል።

የተባበሩት አረብ ኤመሬትስ ባለስልጣናት በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።