ኢትዮጵያ የሰላምና የወዳጅነት እግር ኳስ ዋንጫ ላይ ልትሳተፍ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 3/2011)ኢትዮጵያ በአስመራ በሚካሄደው የሰላምና የወዳጅነት እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ላይ እንደምትሳተፍ አስታወቀች፡፡

የኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን አራት ሀገራት ይካፈሉበታል ተብሎ በሚጠበቀውና በአስመራ አስተናጋጅነት በሚካሄደው “የሠላም እና የወዳጅነት ዋንጫ” ላይ ይሳተፋል ተብሏል።

በየካቲት ወር በአስመራ አስተናጋጅነት በሚካሄደውና በኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ ወጣት ቡድኖች መካከል በሚደረገው ‘የሠላም እና ወዳጅነት ዋንጫ’ ላይ የኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን እንደሚሳተፍ ፌዴሬሽኑ አሳውቋል።

የአራቱን አባል ሃገራት ወዳጅነት እና የዞኑን የእግር ኳስ ትስስር ለማጠናከር ታስቦ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ ውድድር የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን  ከቀናት በኋላ ዝግጅት እንደሚጀምር ተነግሯል።

በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የሰላም ውይይት ተካሂዶ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች መልካም ግንኙነት ከጀመሩ ወዲህ ትብብሩ ይበልጥ እየተጠናከረ መጥቷል።

ይሕ ደግሞ ለአካባቢው ሀገራትም የሰላም ተስፋን ፈንጥቋል።